በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋና በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ በፈጠረው ከፍተኛ ጫና ምክንያት፣ ከ12 በላይ የሚሆኑ አገራት አዲስ የብድር ድጋፍ ለመጠየቅ መገደዳቸውን የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫ አስታወቁ።
ዋና ዳይሬክተሯ በዋሽንግተን ዲሲ በሰጡት መግለጫ፣ በተለይም የሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት ለዚህ ቀውስ ማስታገሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እየፈለጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ድርጅቱ ግምት፣ ጦርነቱ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ድንጋጤ ለመቋቋም ከ20 ቢሊዮን እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ የፋይናንስ ፍላጎት ሊኖር እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ ይህም አዳዲስ የብድር ፕሮግራሞችን መቅረጽን ወይም ነባር የብድር ስምምነቶችን ማሳደግን ሊያካትት ይችላል።
በተለይ የሆርሙዝ የንግድ መስመር መስተጓጎል በዓለም አቀፍ የንግድ ፍሰት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ጆርጂየቫ፣ ጦርነቱ በአፋጣኝ ቢቆም እንኳ የነዳጅና የጋዝ አቅርቦት ስርጭት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ አስገንዝበዋል።
በዚህም ምክንያት የ2026 የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ቀደም ሲል ከተተነበየው 3.1 በመቶ ዝቅ ብሎ ወደ 2.5 በመቶ ሊወርድ እንደሚችልና የነዳጅ ዋጋም በአማካይ እስከ 100 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተተንብዮአል።@SECO


