በኢቢቪ ዘጋቢ
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በአሰሪና በሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችንና የሥራ ክርክሮችን ብቻ የሚመለከት ራሱን የቻለ ልዩ ችሎት እንዲቋቋም መጠየቁን አስታውቋል።
ኮንፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ያቀረበው በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ባለው የፋይሎች መደራረብ ምክንያት የሠራተኛው ፈጣን ፍትሕ የማግኘት መብት እየተጓተተ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።
የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ክርክሮች በአጭር ጊዜ እንዲቋጩ ቢደነግግም፣ በተግባር ግን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጫና ምክንያት ተፈጻሚ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።
የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዲሪብሳ ለገሰ እንደገለጹት፣ ከሕግ ውጪ ከሥራ መፈናቀልና የደሞዝ መከልከል አቤቱታዎች እየበዙ በመመጣታቸው፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ልዩ ችሎት መቋቋሙ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) ውጤታማ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን የሥራ ክርክሮች በልዩ ችሎት ወይም በሽምግልና እንዲፈቱ ይመክራል ሲል የዘገበው አሃዱ ነዉ። @SECO


