የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የመንግስት መስሪያቤቶችን የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች በይፋዊ ድረገጹ ላይ መጫኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የአሁኑ አሰራር አነጋጋሪ ሆኗል።
ለረጅም ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየው የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ድረ ገጽ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወደ አገልግሎት ቢመለስም፣ የ2017/18 በጀት ዓመት ሪፖርቶች ግን ከቀድሞው በተለየ መልኩ ተደራሽ እንዳይሆኑ (ተቆልፈው) መጫናቸው ከፍተኛ ጥያቄ አስነስቷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኦፊሴላዊ ድረ-ገጽ ለአንዳንድ ወራት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ከቆየ በኋላ፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በድጋሚ ወደ ሥራ መመለሱ ታውቋል።
ይሁን እንጂ ድረ-ገጹ ሥራ ቢጀምርም፣ ተቋሙ የ2017/18 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርቶችን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ቀን እና ሰአት ድረስ ማንም በነፃነት ማንበብም ሆነ ማየት በማይችልበት ሁኔታ ቆልፎ መጫኑ ተረጋግጧል።
ይህንን የተመለከቱ የሕግ ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ ይህ የሪፖርቶች ተደራሽ አለመሆን ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው።
በተለይም በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥታዊና የግል ድርጅቶች በእጃቸው ያለን መረጃ ለሕዝብና ለሚዲያ እንዲሰጡ የሚያስገድደውን አዲሱን የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ባጸደቀበት ማግስት እንዲህ ዓይነት አሠራር መዘርጋቱ ሕጉን የሚቃረንና አሻሚ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።
አዲሱ አዋጅ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን በሰፊው የሚያረጋግጥ ቢሆንም፣ በተግባር ግን የፋይናንስ ግልጽነትን የሚያረጋግጡ ቁልፍ የኦዲት መረጃዎች መታገዳቸው አያያዙን ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል።
ይህ በዋና ኦዲተር ድረ-ገጽ ላይ የታየው የመረጃ መገደብ፣ ከዚህ ቀደም ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በስተቀር ሁሉም የግል ሚዲያ ተቋማት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ገብተው እንዳይዘግቡ ከተጣለው እገዳ ጋር ተዳምሮ፣ በአገሪቱ የመረጃ ነፃነትና የፕሬስ ነፃነት ምኅዳር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የዘርፉ ተሟጋቾች ይናገራሉ።
የመንግሥት የፋይናንስ አጠቃቀምና የሀብት ብክነትን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ያላቸው እነዚህ የኦዲት ግኝቶች፣ ተቆልፈው የተጫኑበት ምክንያትና የመሥሪያ ቤቱ ይፋዊ ምላሽ ምን እንደሆነ ለማወቅ የተደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።SECO


