ዋነኛ አላማውም አመራሩ እና ቦርዱ ከስልጣን እንዲለቅ እና እንደልብ በሚታዘዝ አዲስ አካል እንዲተካ ነው ተብሏል
የአንበሳ ባንክ ከፍተኛ አመራር በተለይ ቦርድ ካለፈው አመት መጨረሻ አንስቶ ከፍተኛ መዋከብ እና ጫና እየተደረገበት ነው ሲሉ ውስጥ አዋቂዎች ለኢቢቪ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይህን በቅጡ የተረዳው አይመስልም ሲሉ ነው ውስጥ አዋቂዎች በአንበሳ ባንክ ላይ የተፈጠረውን ውጥንቅት በዝርዝር ያስረዱት፡፡
ምንጮች እንደተናገሩት ቦርድን ጨምሮ የባንኩ አመራር ከስልጣኑ እንዲነሳ በአንዳንድ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አባላት እና ባለሃብቶች ጫና እየተደረገበት ነው ሲሉ ገልፀው፡፡

የ21ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ባለፈው ጥቅምት 2018 ዓም ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ የስብሰባው ውሳኔ እና የቦርድ አባላት ምርጫ ፍትሃዊ አልነበረም የሚሉ ጥቂት ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዎኖች እና የቦርድ አባላት ለተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አቤቱታ ማቅረባቸውን ይገልጻሉ፡፡
የአቤቱታ አቅራቢዎች ዋነኛ ፍላጎት ቦርዱ ፖለቲከኞች በተለይ ትግራይን በተቆጣጠረው ሃይል ፍላጎት በሚዘወሩ አባላት እንዲተካ ነው የሚሉት ውስጥ አዋቂዎች፡፡
ብሄራዊ ባንክ በስብሰባው ሂደት ላይ በቂ ማጣራት አድርጎ ባለፈው ሰኔ 1 ቀን ለሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት የጠቅላላ ጉባኤው ቃለ ጉባኤው እንዲጸድቅ ደብዳቤ ፅፎ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
ነገር ግን በድጋሜ ሰኔ 12 ቀን ሌላ ደብዳቤ በማውጣት አገልግሎቱ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ እንዲያፀድቅ ነገር ግን የቦርድ አባላት ምርጫ ሂደት እንዲቆይ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ቦርዱ ለማእከላዊ ባንኩ አቤቱታ ቢያቀርብም ሰኔ 24 ቀን ብሄራዊ ባንክ የቦርዱን አቤቱታ እንዳልተቀበለ ነው በደብዳቤ የገለጸው፡፡ በተጨማሪም ባለአክሲዎን ጠርታችሁ አዲስ ምርጫ በዚህ ወር አድርጉ ሲል ነው ተቆጣጣሪው ያዘዘው፡፡

ይህን ተከትሎ ከ2 ሶስተኛ በላይ የአክሲዎን ድርሻ ያላቸው የባንኩ ባለሃብቶች ለብሄራዊ ባንክ ቅሬታቸውን ገልጸው ሁኔታውን በይበልጥ ለማስረዳት የባንኩ ገዥ እንዲያናግሯቸው የሚጠይቅ ፔቲሽን ባሳለደፍነው ቅዳሜ ማስገባታቸው ነው የታወቀው፡፡
በተመሳሳይ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ሁኔታውን ገዢው እንዲረዱ በግንባር ቀርበው ማስረዳት እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸው ነው የተገለጸው፡፡
የመረጃ ምንጮች እንደሚገልፁት ባንኩ የባንኩ ባለሃብቶች እና ደንበኞች በዋናነት የሚንቀሳቀሱት ትግራይ ክልል በጥቅምት 2013 ዓም ከተነሳው ግጭት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፡፡
በተለይ ከተሰጠ ብድር መመለስ ጋር በተያያዘአሁንም ያልተቋጨ ጫና ውስጥ ይገኛል፡፡
በአንፃሩ አሁን በቦደርድ መካከል ለተነሳው ልዩነት እና ቦርድ ይውረድ የሚለው ዘመቻ የተጀመረው ቀደም ሲል ከፍተኛ ብድር ወስደው ያልመለሱ የባንኩ ደንበኞች ተጨማሪ ብድር ይሰጣቸው የሚል ግፊት በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ አመራሮች ጭምር በማየሉ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ከብድር በተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ፍቀዱ የሚል ጫና አለ የሚሉት ምንጮች የባንኩ አመራር ለባንኩ ጤንነት የማይበጅ እርምጃ አልወስድም እንዲሁም ከፍተኛ ብድር ላለበት ሰው ተጨማሪ ገንዘብ መፍቀድ በህግ ያስጠይቀናል ማለታቸውን ተከትሎ ልዩነቱ መስፋቱ ነው የሚገለጸው፡፡
እንደመረጃ ምንጮች አሁን ያለው ቦርድ እና የባንኩ አመራር ላይ በተለይ በትግራይ ክልል በሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ጭምር ዘመቻ ተከፍቶ የማዋከብ ስራ እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን፡፡
ዋነኛ አላማውም አመራሩ እና ቦርዱ ከስልጣን እንዲለቅ እና እንደልብ በሚታዘዝ አዲስ አካል እንዲተካ ነው ተብሏል፡፡SECO

