የኢንተርኔት አቅርቦት ቢኖርም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የሞባይል ኢንተርኔት አይጠቀሙም ተባለ

የስማርት ስልክ ውድነት ዋነኛ ምክንያት ነው!

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በሞባይል ኢንተርኔት ያልተጠቀሙ ነገር ግን በሞባይል ብሮድባንድ ኔትወርክ ሽፋን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ከሆነባቸው አገራት መካከል ተመድባለች። ይህንን የገለጸው የGSMA የ2026 የሞባይል ኢንተርኔት ግንኙነት ሁኔታ ሪፖርት ነው።

በሪፖርቱ መሠረት በኢትዮጵያ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሞባይል ብሮድባንድ ሽፋን ባለበት አካባቢ ቢኖሩም የሞባይል ኢንተርኔትን አይጠቀሙም። ይህ ኢትዮጵያን 68 በመቶ የዓለም አቀፉን የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም ክፍተት ከሚወክሉ 20 አገራት መካከል እንድትገኝ እንዳደረጋት ነው ትላንት የወጣው አዲስ ሪፖርት ያተተው፡፡

የኢትዮጵያ የአጠቃቀም ክፍተት ከምስራቅ አፍሪካ ጎረቤቶቿ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ እንደሚበልጥ ነው ሪፖርቱ ያሳየው፡፡

በሪፖርቱ መሰረት በቅደም ተከተል በታንዛኒያ ወደ 50 ሚሊዮን፣ በዩጋንዳ 40 ሚሊዮን እና በኬንያ 40 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በሞባይል ብሮድባንድ ሽፋን ውስጥ ቢሆኑም የሞባይል ኢንተርኔትን አይጠቀሙም።

በ2025 ከሰሃራ በታች አፍሪካ ከሌሎች የዓለም ክልሎች ዝቅተኛው የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም ተመዝግቧል ያለው ሪፖርቱ፤ በክፍለ አህጉሩ 25 በመቶ ብቻ የስልክ ተጠቃሚ የሞባይል ኢንተርኔትን የመጠቀም እድል እንደነበረው ነው ያከለው፡፡

የአጠቃቀም ክፍተቱ 66 በመቶ መሆኑን ጠቅሶ የኢንተርኔት የሽፋን ክፍተቱ ግን 9 በመቶ ነበር ሲል ነው ያከለው።

ይህም ዋነኛው ችግር ኔትወርክ አለመሆኑን ያሳያል ያለው ሪፖርቱ፡፡ ዋነኛው ጉዳይ ያለውን ኔትወርክ ሰዎች ወደ አጠቃቀም መቀየር አለመቻላቸው መሆኑን ያሳያል።

በዓለም ደረጃ በ2025 4.8 ቢሊዮን ሰዎች፣ ወይም የዓለም ህዝብ 59 በመቶው፣ በራሳቸው የስልክ ቀፎ የሞባይል ኢንተርኔትን ተጠቅመዋል የተባለ ሲሆን።

በተቃራኒው 3.1 ቢሊዮን ሰዎች የሞባይል ብሮድባንድ ሽፋን ባለበት አካባቢ ቢኖሩም የሞባይል ኢንተርኔትን አልተጠቀሙም። ተጨማሪ 270 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከሞባይል ብሮድባንድ ሽፋን ውጭ ነበሩ በተጠቀሰው አመት።

GSMA በሪፖርቱ እንደጠቀሰው ለኢንተርኔት ምቹ ስልክ በተመጣጣኝ ዋጋ አለመኖር በስልክ ኢንተርኔት ላለመጠቀም ዋነኛ ምክንያት ነው ብሏል፡፡

የዳታ ዋጋም ደግሞ ሌላው ተግዳሮት ነው ተብሏል።

ከሰሃራ በታች አፍሪካ 20 ጊጋባይት የሞባይል ዳታ በአማካይ ከወር ገቢ 14 በመቶ ጋር የሚመጣጠን ወጪ ያስወጣል የተባለ ሲሆን። ይህም በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ አገራት ከተመዘገበው 3.2 በመቶ መካከለኛ ደረጃ እጅግ ከፍ ያለ ነው።

ሪፖርቱ የገጠርና የከተማ ህዝብ እንዲሁም የሴቶችና የወንዶች የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም ልዩነትንም አመልክቷል። በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ አገራት የገጠር አዋቂዎች ከከተማ አዋቂዎች 28 በመቶ ያነሰ የሞባይል ኢንተርኔት የመጠቀም ዕድል አላቸው።

ሴቶችም ከወንዶች 12 በመቶ ያነሰ የመጠቀም ዕድል ሲኖራቸው፣ ሴቶች ከአዋቂዎች የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም ክፍተት 58 በመቶውን ይወክላሉ።

በመሠረተ ልማት ረገድ ግን ንኡስ አህጉሩ እድገት እያሳየ መሆኑ ተመላክቷል።

በ2025 በሰሃራ በታች አፍሪካ 81 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በ4G ኔትወርክ ሽፋን ውስጥ ነበር። በዓለም ደረጃም የ5G ሽፋን እየሰፋ ቢሆንም፣ የስማርት ቀፎዎች እና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ዋጋ አሁንም ኔትወርክ ከመኖሩ ወደ ተጨባጭ አጠቃቀም ለመሸጋገር ዋና እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ብሏል ሪፖርቱ። SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 220 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ አወጣ

​የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘጠኝ ክፍለ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

Popular Categories