ከስድስት የአፍሪካ አገራት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የቪዛ ማመልከቻ የሚያስገቡ መንገደኞች፣ አዲስ በተጣለው የ250 ዶላር “የቪዛ ታማኝነት ክፍያ” ምክንያት ከፍተኛ ወጪና ጥብቅ ፍተሻ እየተጋረጠባቸው መሆኑ ተገለጸ።
እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2025 በይፋ መተግበር የጀመረው ይህ አዲስ መመሪያ፣ አጠቃላይ የቪዛ ማመልከቻ ወጪን ከ435 ዶላር በላይ ከፍ አድርጎታል።
አዲሱ መመሪያ ተግባራዊ የሚሆንባቸው አገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ጋና እና ዚምባብዌ ሲሆኑ፣ መንገደኞቹ ከክፍያው በተጨማሪ ጥብቅ የዲጂታል እና የባዮሜትሪክ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ ይጠበቅባቸዋል።
መስፈርቶቹ የ5 ዓመት የሶሻል ሚዲያ ታሪክን፣ የ10 ዓመት የኢሜል መረጃዎችን እና በሞባይል መተግበሪያ የሚታገዝ የፊት ገጽታ ማረጋገጫ ማቅረብን ያካትታሉ።
የአሜሪካ መንግሥት ለውጡን ያደረገው የቪዛ ማጭበርበርን ለመከላከል እና የቪዛ ጊዜያቸው አልፎ በአገሪቱ የሚቆዩ ሰዎችን ለመቆጣጠር መሆኑን ቢገልጽም፣ ውሳኔው ለአፍሪካውያን አመልካቾች ከባድ የገንዘብ እና የቢሮክራሲ ጫና መፍጠሩ ተነግሯል።
አጠቃላይ 439 ዶላር የሚደርሰው ክፍያ 185 ዶላር ለመደበኛ የቪዛ ማመልከቻ፣ 250 ዶላር ለታማኝነት ክፍያ እና 4 ዶላር ለተጓዦች መረጃ ማቀነባበሪያ የሚውል ነው።
ይህንን ተከትሎ እንደ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር ያሉ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት በተመሳሳይ የአሜሪካ ዜጎች ላይ ጥብቅ የቪዛ መስፈርቶችን በመጣል የአፀፋ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተመልክቷል። ውሳኔው በተለይ ተማሪዎች፣ ቱሪስቶች እና የንግድ ተጓዦች ላይ የጊዜ መጓተትና የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድር ተንታኞች ገልጸዋል።@SECO


