የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ባወጣው የ2026 የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ እና ትንበያ ሪፖርት፣ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ወደ 2.7 በመቶ ዝቅ እንደሚል አስታውቋል።
ይህ አኃዝ በ2025 ከነበረው የ2.8 በመቶ ግምት መጠነኛ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሱት የአሜሪካ የንግድ ታሪፍ መጨመር፣ የፖሊሲ አለመረጋጋቶች እና እየናሩ የመጡ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ናቸው።
ምንም እንኳን የዓለም ኢኮኖሚ እድገት በ2027 ወደ 2.9 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ ቢጠበቅም፣ አሁንም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት ከነበረው አማካይ የ3.2 በመቶ እድገት በታች መሆኑ ተገልጿል።
እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፣ የታላላቅ ሀገራት ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ያልፋል። የአሜሪካ የኢኮኖሚ እድገት በ2026 ወደ 2 በመቶ መጠነኛ ጭማሪ ያሳያል ተብሎ ቢገመትም፣ የቻይና ኢኮኖሚ ግን በ2025 ከነበረበት 4.9 በመቶ ወደ 4.6 በመቶ ዝቅ ይላል ተብሏል።
በተመሳሳይ የአውሮፓ ህብረት ኢኮኖሚ በከፍተኛ የታሪፍ ጫና እና በጂኦ-ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት የወጪ ንግዱ ስለሚጎዳ፣ እድገቱ ወደ 1.4 በመቶ ዝቅ ሊል እንደሚችል ተተንብዮአል።
የጃፓን ኢኮኖሚም ቢሆን ከታሪፍ ጋር በተያያዘ በተለይም በመኪና ምርት ዘርፍ በሚገጥመው ተጽዕኖ ሳቢያ እድገቱ 0.9 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሌላ በኩል፣ ሪፖርቱ በታዳጊ ሀገራት በተለይም በምስራቅ አፍሪካ መልካም የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመዘገብ አመልክቷል። ኢትዮጵያ፣ ባንግላዴሽ እና ታንዛኒያ ጠንካራ አፈጻጸም ከሚያሳዩ ሀገራት መካከል ተጠቅሰዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ እና ኬንያ በ2026 የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ የ6.3 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ተተንብዮላታል። ይህ እድገት በማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት እና በግብርና ምርታማነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ቢገለጽም፣ ተመድ ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች አሁንም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ዋነኛ ስጋቶች መሆናቸውን አሳስቧል።@SECO


