በ2025 የፈረንጆቹ ዓመት በአሜሪካ የተፈጥሮ ጋዝ የገበያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የኤል.ኤስ.ኢ.ጂ መረጃዎች አመልክተዋል። ይህ ጭማሪ የታየው እጅግ ዝቅተኛ የዋጋ መጠን ተመዝግቦበት ከነበረው የ2024 ዓመት በኋላ ሲሆን፣ በሄንሪ ሀብ የሚለካው የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በዋጋ ግሽበት ታስቦም ቢሆን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የላቀ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም ለተጠቃሚዎች እና ለኢንዱስትሪዎች የኃይል ወጪ መጨመር አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ለዚህ የዋጋ ጭማሪ በምክንያትነት የተጠቀሱት በ2025 የታየው የተፈጥሮ ጋዝ ምርት መቀነስ እና በተቃራኒው ደግሞ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የሚውለው ጋዝ ፍላጎት መጨመር ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) ወደ ውጭ የመላክ አቅም ማደግ እና የዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት መጨመር በአገር ውስጥ ያለውን የዋጋ መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በ2024 ዓመት ዋጋው እጅግ ዝቅተኛ የነበረው በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ የምርት ክምችት እና መጠነኛ በነበረ የአየር ሁኔታ ምክንያት እንደነበረ ይታወሳል።
ይህ በ2025 የታየው የዋጋ ለውጥ በዓለም አቀፍ የኃይል ገበያ ላይም የራሱን ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። በተለይም አሜሪካ ወደ አውሮፓ እና እስያ የምትልከው የተፈጥሮ ጋዝ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ የአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። የዘርፉ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፣ በቀጣይ ዓመታትም የምርት እና የፍላጎት አለመመጣጠን በዋጋው ላይ መለዋወጥን ሊያስከትል ይችላል።@SECO


