የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ በላኩት ደብዳቤ፤ በዓባይ ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ውዝግብ ለመፍታት አሜሪካ ዳግም ሽምግልና ለመጀመር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በዚህ ደብዳቤያቸውም አስተዳደራቸው የውሃ ክፍፍል ጥያቄን በኃላፊነት ስሜት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሀገር የዓባይን ውድ ሀብት ብቻውን መቆጣጠርና ጎረቤቶቹን መጉዳት የለበትም ሲሉ አረጋግጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ ውዝግቡ ወደ ከፍተኛ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመራ ተስፋቸውን ገልጸው፣ ይህን ጉዳይ መፍታት በአጀንዳቸው ውስጥ በቀዳሚነት የሚቀመጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአሜሪካው አዲስ የመፍትሄ አቀራረብ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ግብጽ እና ሱዳን በድርቅ ወቅት ሊተነበይ የሚችል የውሃ ልቀት ዋስትና እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታመነጭ የሚፈቅድ ነው።
ትራምፕ በዚሁ ሃሳባቸው ላይ ኢትዮጵያ ከምታመነጨው ኃይል መካከል የተወሰነውን ለጎረቤቶቿ በነጻ እንድትሰጥ ወይም እንድትሸጥ የጠቆሙ ሲሆን፣ በትክክለኛ ቴክኒካዊ እውቀት፣ ፍትሃዊ ድርድር እና በጠንካራ የአሜሪካ የክትትል ሚና የታገዘ ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ በደብዳቤያቸው ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ላደረጉት የመሪነት ሚና እና ከጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ የነበሩትን የደህንነት እና ሰብአዊ ተግዳሮቶች በመወጣታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተላከው ደብዳቤ ለቀጣናዊ መሪዎች በግልባጭ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ እና የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ይገኙበታል።@SECO


