የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ አሁን ላይ የዴንማርክ የራስ ገዝ ግዛት የሆነችውን ግሪንላንድን “ሙሉ በሙሉ ለመግዛት” ስምምነት ላይ እስክትደርስ ድረስ፣ በስምንት የአውሮፓ አገራት ላይ የንግድ ታሪፍ መጣላቸውን በይፋ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ በ”ትሩዝ ሶሻል” ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ መሠረት፣ በዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ኔዘርላንድስ እና ፊንላንድ ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ከፌብሩዋሪ 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ አሜሪካ ግሪንላንድን ለመግዛት የሚያስችላትን ስምምነት ካላገኘች ደግሞ ይህ ታሪፍ ሰኔ 1 ቀን ወደ 25 በመቶ ከፍ እንደሚል አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ለስትራቴጂካዊ ስፍራዋ እና ለከፍተኛ የማዕድን ክምችቷ እጅግ አስፈላጊ መሆኗን በመጥቀስ፣ ግዛቱን በገንዘብ ለመግዛት አልፎ ተርፎም ኃይል ለመጠቀም እንደማያቅማሙ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ የአውሮፓ ኅብረት ለአሜሪካ ውሳኔ የሚሰጠውን ምላሽ እያጤነ መሆኑን በመግለጽ፣ ኅብረቱ የአባል አገራቱን ሉዓላዊነትና ዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር ጠንካራና የጋራ አቋም እንደሚይዝ አስታውቀዋል።
ይህ የታሪፍ ውሳኔ የተላለፈው ዴንማርክ በአርክቲክ አካባቢ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን ለመጠበቅ በጠየቀችው መሠረት የአውሮፓ አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ግሪንላንድ በላኩ ማግስት መሆኑ ውጥረቱን ይበልጥ አባብሶታል።
ምንም እንኳ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የግዢ ፍላጎታቸውን ቢገልጹም፣ ግሪንላንዳውያን ግን ሐሳቡን በጽኑ ይቃወማሉ፤ እ.ኤ.አ በጥር 2025 በወጣ የሕዝብ አስተያየት ጥናት መሠረት 85 በመቶ የሚሆኑት ግሪንላንዳውያን ከአሜሪካ ጋር የመቀላቀልን ሐሳብ እንደማይደግፉ ታውቋል።@SECO


