የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመግዛት ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ በአውሮፓ አገራት ላይ የጣሉት የታሪፍ ማስፈራሪያ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል ለዘመናት የቆየውን ወዳጅነት ወደ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከተቶታል።
ኒውዮርክ ታይምስ ባወጣው ትንታኔ፣ አውሮፓ አሁን ላይ ሁለት አስቸጋሪ ምርጫዎች ከፊቷ ተደቅነዋል፤ እነሱም ወይ የአሜሪካን የንግድ ጦርነት በዝምታ መቀበል አልያም “የንግድ ባዙካ” የተሰኘውን ጠንካራ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ናቸው።
ይሁን እንጂ አውሮፓ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ መግባት ብትፈልግም፣ በሌላ በኩል ለደኅንነቷ በኔቶ በኩል እና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለምታገኘው ድጋፍ በአሜሪካ ላይ ጥገኛ መሆኗ እጅንና እግርን የሚያስር ሆኖባታል።
የብራሰልሱ የኢኮኖሚ ተንታኝ ጃኮብ ኪርክጋርድ ሁኔታውን ሲገልጹ “ወይ የንግድ ጦርነት ውስጥ እንገባለን፣ አልያም እውነተኛ ጦርነት ውስጥ እንሆናለን” በማለት የአውሮፓን የፖለቲካ አጣብቂኝ አመልክተዋል።
ይህንን ተፅዕኖ ለመቋቋም የአውሮፓ መሪዎችና ተቋማት ተከታታይ የተቃውሞ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል።
የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ትራምፕና ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ባለፈው ክረምት የተፈራረሙትን የንግድ ስምምነት ለማፅደቅ የጀመሩትን ሂደት ማገዳቸውን አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ አውሮፓ በፖለቲካዊ ጫናዎች ለሚመጡ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ያዘጋጀችውን “የአጸፋ መሣሪያ” ወይም “ባዙካን” በመጠቀም፣ እንደ ጎግልና አፕል ባሉ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ገደብ ለመጣል እያሰበች መሆኑ ተገልጿል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ማክሮን እና የስዊድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን በዛቻና በማስፈራሪያ እንደማይንበረከኩ ሲገልጹ፣ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመርም የታሪፍ ውሳኔው “ፍጹም ስህተት” መሆኑን በመግለጽ ከትራምፕ ጋር በዳቮስ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።
በአንጻሩ የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ አሜሪካ ግሪንላንድን መግዛቷ ለአውሮፓም ሆነ ለአሜሪካ ምርጥ ምርጫ መሆኑን ገልጸው፣ ግዛቱ በኃይል ቢወሰድ እንኳ አውሮፓውያን ውሎ አድሮ ሐሳቡን እንደሚቀበሉት ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የግሪንላንድ ሕዝብ ለነፃ ትምህርትና ለጤና አገልግሎታቸው ዋስትና የሚሰጣቸውን የዴንማርክ አስተዳደር የሚመርጡ በመሆኑ ከአሜሪካ ጋር መቀላቀልን አይፈልጉም። ይህን ተለዋዋጭ ሁኔታ ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች ዛሬ እሁድ አመሻሽ ላይ በብራሰልስ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ቀጣዩን የጋራ እርምጃ ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል።@SEECO


