በበርሊን እየተካሄደ ያለውን 100ኛው ዓለም አቀፍ የ”አረንጓዴ ሳምንት” የግብርና ኤግዚቢሽን ተከትሎ በወጣ ጥናት፤ በጀርመን የሚገኙ አነስተኛ እና መካከለኛ አርሶ አደሮች ከሥራ ውጪ የመሆን አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
ምንም እንኳን ላለፉት ጥቂት ዓመታት የሸማቾች የምግብ ዋጋ በ35 በመቶ ቢጨምርም፣ ይህ ገቢ ግን ወደ አርሶ አደሩ አልደረሰም።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አራት ግዙፍ የችርቻሮ ኩባንያዎች የአቅርቦት ሰንሰለቱን ተቆጣጥረው አርሶ አደሩ ዝቅተኛ ትርፍ ብቻ እንዲያገኝ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ነው። በተጨማሪም የነዳጅ ዋጋ መናር እና የአውሮፓ ኅብረት ከደቡብ አሜሪካ አገራት ጋር የደረሰው የንግድ ስምምነት በጀርመን አርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።
የአገሪቱ ፖለቲከኞችም ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ሐሳቦችን እያቀረቡ ይገኛሉ። ገዥው የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ መሠረታዊ ምግቦች በቅናሽ እንዲሸጡ ሐሳብ ቢያቀርብም፣ የግብርና ሚኒስትሩ አሎይስ ራይነር ግን “ምግብ በቅናሽ መሸጥ የለበትም” በሚል ውድቅ አድርገውታል።
በሌላ በኩል እንደ ታፈል (Tafel) ያሉ የምግብ ባንኮች የሕዝቡን የገቢ አቅም ማሻሻል የተሻለ መፍትሔ እንደሆነ ይሞግታሉ። እስከ ጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በግብርናው ዘርፍ ያለውን ሚና የሚዳስሱ ምክክሮችም እየተካሄዱ ይገኛሉ።@SEECO


