የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል የሆነው አራተኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ግምገማ መጠናቀቁን አስታወቁ።
እንደ መግለጫው ከሆነ፣ ግምገማው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለችበት ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አፈጻጸም መጀመሪያ ላይ ከታቀደው በላይ ጠንካራ ሆኖ ተገኝቷል።
በግምገማው ወቅት ሁሉም በቁጥር የሚለኩ የአፈጻጸም መስፈርቶች መሟላታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ቁልፍ የኢኮኖሚ ግቦችም ከታቀደው በላይ መከናወናቸው ተመልክቷል።
ይህን ተከትሎም፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የ261 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲለቀቅ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህም በአሁኑ ስምምነት መሠረት ለኢትዮጵያ የተለቀቀውን ጠቅላላ የገንዘብ መጠን ወደ 2.18 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ አድርጎታል።
መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚታዩ አራት ዋና ዋና ስኬቶችን ለይቶ ጠቅሷል።
በተለይም በውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ የተደረገው ማሻሻያ እና ወደ ገበያ መር ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር፣ በኢኮኖሚው ላይ እምነት ከመመለሱም በላይ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ማሳደጉ ተገልጿል።
ከዕዳ ዘላቂነት ጋር በተያያዘም፣ በቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ መሠረት ከይፋዊ አበዳሪዎች ጋር የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት፣ በኢኮኖሚው ላይ የሚታየውን እርግጠኛ አለመሆን በመቀነስ ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት ትልቅ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።@SECO


