ባንኮች ለተመረጡ የገቢ ዕቃዎች የብድር ሰነድ (Letters of Credit) ይሁን ሌላ ክፍያ መንገድ ሲፈቅዱ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተመንን እንደ አመላካች ዋጋ እንዲጠቀሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በሐምሌ 2016 ዓ.ም ተግባራዊ ያደረገውን የውጭ ምንዛሪ መመሪያን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ያስታወው ባንኩ መመሪያው ባንኮች ከደንበኞቻቸው ጋር በመደራደር የውጭ ምንዛሪ መሸጫና መግዣ ተመኖችን መወሰን እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡
በተጨማሪም ባንኮች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረው ዝቅተኛ የገቢ ዕቃዎች ዋጋ መመሪያ (Minimum Price Directive) (በመሰረዙ፣ አሁን ግን በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የገቢ የዕቃዎችን ዋጋ ትክክለኝነት የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ፣ ባንኮች ለብድር ሰነድ (Letters of Credit) የሚጠቀሙባቸው ዋጋዎች ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የማጣቀሻ ዋጋዎች ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
የዋጋ ልዩነቶቹን ለማስተካከልና የዋጋ ማጣቀሻዎችን ለማጣጣም ሁሉም ባንኮች ከጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም (January 27, 2026) ጀምሮ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተመንን እንደ አመላካች ዋጋ ይጠቀማሉ ያለው ባንኩ ይህም በባንክ ሥርዓቱና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት ለማስወገድና የውጭ ምንዛሪ መረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አስታውቋል።@SECO


