የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረካቸውን በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄዱ ነው
የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደገለጹት በያዝነው 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 640 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 709 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል::
ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥም የሀገር ውስጥ 366 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከቀረጥና ታክስ 342 ቢሊየን ብር ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ተቋሙ በታክስ ስርዓቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 61.49 ቢሊየን ብር ለክልሎች እና ለከተማ መስተዳደሮች ለማስተላለፍ ዕቅድ ተይዞ ብር ከ79.85 ቢሊየን ብር በላይ በማስተላለፍ የዕቅዱን 130 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተገልጿል።
በዚሁ መድረክ የጉምሩክ ኮሚሽን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም በጉምሩክ ኮሚሽን የቀረበ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎችና ህገ ወጥ ገንዘብ መያዝ ተችሏል፡፡
በተከናወነው የኮንትሮባንድ መከላከል ስራ የተያዙት እቃዎች ግምታዊ ዋጋቸው ብር 12 ቢሊየን 132 ሚሊየን 976 ሺ 285 የሚገመቱ የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና ብር 918 ሚሊየን 609ሺ 710 የሚገመቱት ደግሞ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና ህገ-ወጥ ገንዘብ ከሃገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ ተነግሯል፡፡
አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በገቢ ኮንትሮባንድ ከብር 7 ቢሊየን ብር በላይ ወይም 64.45 በመቶ ብልጫ፣ እንዲሁም በወጪ ኮንትሮባንድ ከብር 1 ቢሊየን ብር በላይ ወይም የ41.6 በመቶ ጉድለት ያለው ሲሆን በአጠቃላይ የ45.82 በመቶ ብልጫ ተመዝግቧል፡፡ @SECO


