የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) በ2026 የአለም ኢኮኖሚ የ3.3 በመቶ ጠንካራ እድገት እንደሚያስመዘግብ ቢተነብይም፣ ይህን ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እንደ ቀላል መውሰድ እንደማይገባ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂቫ በዳቮስ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት፣ የአለም ኢኮኖሚ በታሪፍ ጫናዎችና በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ውስጥ አልፎ አሁንም ድረስ ጠንካራ ሆኖ መቀጠሉ የሚደነቅ ቢሆንም፣ ይህ መቋቋም በዘላቂነት ይቀጥላል ተብሎ ሊታመን አይገባም።
እንደ ጆርጂቫ ገለጻ፣ ለአሁኑ እድገት አራት ዋና ዋና ምክንያቶች ያሉ ሲሆን እነሱም መንግስታት ጣልቃ ገብነታቸውን ቀንሰው የግል ዘርፉን ማበረታታቸው፣ የንግድ ግጭቶች በኢኮኖሚው ላይ ያመጡት ተፅዕኖ ዝቅተኛ መሆኑ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ እየፈሰሰ ያለው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኢንቨስትመንት እና የማዕከላዊ ባንኮች ከፖለቲካ ጫና ነፃ መሆናቸው ናቸው።
ይሁን እንጂ ዳይሬክተሯ በተለይ በማዕከላዊ ባንኮች ነፃነት ላይ እያጋጠመ ያለው ስጋት እና በዋይት ሃውስና በፌዴራል ሪዘርቭ መካከል ያለው ውጥረት ለወደፊቱ የኢኮኖሚ መረጋጋት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። የአለም ኢኮኖሚ በ2027ም በተመሳሳይ የ3.3 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ዘላቂ ጥንካሬን ለማረጋገጥ ጠንካራ ተቋማዊ ፖሊሲዎችን መከተል ወሳኝ መሆኑን IMF አሳስቧል።@SECO


