ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ የንግድ ምክር ቤት የ2026 የዓመቱ “የኢንዱስትሪ ኢነርጂ ፕሮጀክት” (Industrial Energy Project of the Year) ተብሎ ተመረጠ።
ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም በጋና አክራ ኬምፐንስኪ ጎልድ ኮስት ሆቴል በተካሄደው የዕውቅና ሥነ-ሥርዓት ላይ ሽልማቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በመወከል በጋና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ የሚሲዮን መሪ አምባሳደር አሣየ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ተቀብለዋል።

የአፍሪካ የንግድ ሽልማት ዳይሬክተር መሀሙዱ ሃያቱ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ሊሸለም የቻለው ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሽግግር፣ ለቀጣናዊ የንግድና የኤሌክትሪክ ትስስር እያበረከተ ያለውን የጎላ አስተዋጽኦ እና የታየበትን የላቀ የፕሮጀክት አመራር ሚና ዕውቅና ለመስጠት ነው።
ግድቡ ለከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ፣ ለግብርና ማቀነባበሪያ እና ለኢንዱስትሪ የእሴት ሰንሰለቶች መሠረት የጣለ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑም በዕለቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው፣ ሽልማቱ አፍሪካውያን በራሳቸው ሀብትና ጥረት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።@SECO


