የቦስተን ኮንሰልቲንግ ግሩፕ ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት፣ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት የዋጋ ንረትና የገንዘብ ምንዛሬ መዋዠቅ የሚታይበት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ወቅት ላይ ብትገኝም፣ ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ለወደፊቱ ያለው ከፍተኛ ተስፋ የንግድ እንቅስቃሴውን እየቀየረው ይገኛል።
ምንም እንኳን በአህጉሪቱ ያለው የሸማቾች መተማመን ከ2018 ወዲህ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ፣ በናይጄሪያ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሞሮኮና በግብፅ የሚገኙ ከ18 እስከ 27 ዓመት የሆናቸው 119 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸው እንደሚሻሻል በጽኑ ያምናሉ።
ይህ የ”ወጣቶች ፓራዶክስ” ተብሎ የተጠራው ሁኔታ፣ ወጣቶቹ አሁን ካሉበት የገንዘብ እጥረት ይልቅ ለወደፊት ብሩህ ተስፋቸው ትኩረት በመስጠት፣ እንደ ምግብና የግል እንክብካቤ ላሉ ጉዳዮች ካላቸው ገቢ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲያወጡ እያደረጋቸው ነው።
ይህ አዲስ ትውልድ ከቀደሙት ትውልዶች በተለየ ለዋጋ ቅናሽ ብሎ የምርት ጥራትን የማይሰዋ ሲሆን፣ በዲጂታል አማራጮች የታገዘ አዲስ የሸመታ ዘይቤንም እየተከተለ ይገኛል። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሸማቾች ዕቃዎችን በአካል ከመግዛታቸው በፊት በኢንተርኔት፣ በተለይም እንደ ቲክቶክ (TikTok) እና ኢንስታግራም ባሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች መረጃዎችንና ምክሮችን እንደሚፈልጉ ጥናቱ አመልክቷል።
በተጨማሪም እንደ ሞባይል ባንኪንግ ያሉ አዳዲስ የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች ወጣቶች መደበኛ የባንክ ሂሳብ ሳይኖራቸው የብድርና የክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻላቸው፣ ለኢኮኖሚ እድገቱ ትልቅ አቅም እየሆኑ ነው። ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ የንግድ ድርጅቶች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከወጣቱ ትውልድ ጋር እምነትን መገንባት ከቻሉ፣ ለወደፊቱ በገበያው ውስጥ ዘላቂ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ ይችላሉ።@SECO


