ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ግሩፕ የ“ሆራይዘን” ድንበር ተሻጋሪ የፋይበር መስመር ዝርጋታን እውን ለማድረግ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት በጅቡቲ ነው የተፈራረሙት።
ስምምነቱ ከፍተኛ አቅም ያለው ድንበር ተሻጋሪ የኦፕቲካል ፋይበር መሠረተ ልማት ለመዘርጋት እና የቀጣናውን ዲጂታል ትስስር ወደ ላቀና አስተማማኝ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ “በኢትዮ ቴሌኮም፣ በጅቡቲ ቴሌኮም እና በሱዳቴል ግሩፕ መካከል የተደረገው ይህ የሦስትዮሽ ስምምነት፤ የጋራ የዲጂታል የወደፊት እጣ ፈንታችንን ለመገንባት የሚያስችል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ጠንካራና ከፍተኛ አቅም ያለው እንዲሁም አፍሪካን በዲጂታል የሚያስተሳስር የኮኔክቲቪቲ ኮሪደር ለመፍጠር የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ጠቁመው በተለይ የጅቡቲን የባሕር ውስጥ የፋይበር ኬብሎች በኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ከሱዳን ጋር በማስተሳሰር፤ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ አስተማማኝ የየብስ መስመር ተግባራዊ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ አገራትን በትብብር የሚያስተሳስር፣ ኢኮኖሚን የሚያጠናክር እና ቀጣናችንን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ውስጥ ጠንካራ እና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መግቢያ (Gateway) የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የጅቡቲ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር መሐመድ አሶዌ ቡህ በበኩላቸው፤ “የሆራይዘን ፕሮጀክት ለአገራቱ የጋራ እድገትና ብልጽግና ያለንን ራዕይ መሰረት በማድረግ በቀጠናው የቴሌኮም መሠረተ ልማትና ትስስር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት አእንደሆነ ተናግረወል፡፡
የሱዳቴል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ማግዲ ኤም. አብደላ ታሃ “የሆራይዘን ፕሮጀክት ከመሠረተ ልማት ግንባታነት ባሻገር በአፍሪካ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች መካከል ለሚደረግ የፈጠራ አጋርነት ህያው ምስክር እነደሆነ አስረድተዋል፡፡@SECO


