በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና ግለሰቦች ላይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።
ማዕቀቡ በሱዳን መደበኛ ጦር እና በፈጣን ደጋፊ ኃይሎች ውስጥ የሚገኙ ስድስት ግለሰቦችን ያካተተ ሲሆን፣ እነዚህም ግለሰቦች በንጹሃን ላይ ግፍ በመፈጸም፣ ጾታዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም እና ከውጭ ሀገራት ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በማስገባት ጦርነቱ እንዲፋፋም በማድረግ የሚጠረጠሩ ናቸው።
በማዕቀብ ከተመቱት መካከል በጃዚራ ግዛት ውስጥ ለተፈጸሙ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች ተጠያቂ የሆኑት የሱዳን ጋሻ ኃይሎች መሪ አቡ አቅላ ካይካል እና የፈጣን ደጋፊ ኃይሎች አዛዥ ሁሴን ባርሻም ይገኙበታል።
በተጨማሪም የቀድሞ የኮሎምቢያ ወታደሮችን ለጦርነት በመመልመል የተሳተፉ ግለሰቦች እና ለፈጣን ደጋፊ ኃይሎች በሕገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው የአል-ካሊጅ ባንክ ዳይሬክተርም በማዕቀቡ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቬት ኩፐር ከሱዳን ተፈናቅለው ቻድ ድንበር የሚገኙ ስደተኞችን ከጎበኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ግፍ እንዲፈጸም ለፈቀዱ ወታደራዊ አዛዦችና ከጦርነቱ ትርፍ ለሚያግበሰብኩ አካላት የሚከፍሉት ዋጋ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።@SECO


