የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ እስራኤል ለሶማሊላንድ ነፃነት የሰጠችውን ዕውቅና በጽኑ በመቃወም፣ ግዛቱ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዶሃ ከሚገኘው አልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የእስራኤልን እርምጃ “ህገ-ወጥ እና የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚጥስ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ሶማሊላንድ ውስጥ የጦር ሰፈር የመመስረት ዕቅድ ካለ ሶማሊያ ይህንን እንደማትፈቅድና ራሷን ለመከላከል እንደምትጋፈጥ አስታውቀዋል።
የውጥረቱ መነሻ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ታህሳስ ወር ሶማሊላንድን እንደ ገለልተኛ ሀገር ዕውቅና መስጠታቸው ሲሆን፣ ይህም እስራኤልን ለግዛቱ ዕውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር አድርጓታል።
ምንም እንኳን እስራኤልና ሶማሊላንድ በይፋ ወታደራዊ ስምምነት መኖሩን ቢክዱም፣ አንዳንድ የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ግን ጉዳዩ በውይይት ደረጃ ላይ መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ይህ እርምጃ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር የንግድ መስመር ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር ስጋታቸውን ገልጸዋል። አብዛኞቹ የአፍሪካ እና የአረብ ሀገራት መንግስታት የሶማሊያን አንድነት በመደገፍ የእስራኤልን እርምጃ ሲቃወሙ፣ አዲሱ የሶማሊላንድ መሪ አብዲራህማን መሀመድ አብዱላሂ (ሲሮ) ግን ዕውቅናውን በአዎንታዊነት ተቀብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን የሶማሊላንድን ጉዳይ በድጋሚ እየመረመረች መሆኑን ቢገልጹም፣ እስካሁን ይፋዊ የፖሊሲ ለውጥ አልተደረገም። ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ. በ1991 ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን ብታስተዳድርም፣ የእስራኤል ዕውቅና በቀጣናው አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ ቀስቅሷል።@SECO


