የቻይናው የቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባንያ ሁዋዌ እ.ኤ.አ. በ2025 የዓመታዊ ገቢው ከ880 ቢሊዮን ዩዋን (127 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) በላይ መድረሱን አስታወቀ።
ኩባንያው ይፋ እንዳደረገው፣ ይህ አኃዝ በኩባንያው ታሪክ እ.ኤ.አ. በ2020 ከተመዘገበው ከፍተኛ ገቢ (891 ቢሊዮን ዩዋን) ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት ነው።
የሁዋዌ የቦርድ ሰብሳቢ ሃዋርድ ሊያንግ ሁዋ በጓንግዶንግ በተካሄደ የልማት ኮንፈረንስ ላይ እንደገለጹት፣ ኩባንያው የአሜሪካን የንግድ ማዕቀቦች በመቋቋም የተረጋጋ የሥራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያላቸውን ምርቶችና አገልግሎቶች ማቅረቡን ቀጥሏል።
በተለይም በስማርት ስልክ ዘርፍ ሁዋዌ በቻይና ገበያ የ16.4 በመቶ ድርሻ በመያዝ የአሜሪካውን አፕል (16.2 በመቶ) በመብለጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ይህ ስኬት ኩባንያው እ.ኤ.አ. ከ2020 በኋላ በቻይና የስማርት ስልክ ገበያ መሪነቱን ሲረከብ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ይህም ለአሜሪካ ማዕቀብ እጅ አለመስጠቱንና በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያሳየ ያለውን ጥንካሬ የሚያመላክት መሆኑ ተገልጿል።
ሁዋዌ በ2024 የነበረው ገቢ ከ860 ቢሊዮን ዩዋን በላይ የነበረ ሲሆን፣ የ2025 ውጤት ኩባንያው ከገጠሙት ፈተናዎች ወጥቶ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው እየተመለሰ መሆኑን የሚያሳይ ነው።@SECO


