በኢቢቪ ዘጋቢ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአርሶ አደሮችን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና የአቀናባሪዎችን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየሰራ ባለው የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አማካኝነት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
በዚህም መሠረት በ2017 በጀት ዓመት ለአርሶ አደሮች፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለዩኒየኖችና ለአቀናባሪዎች 375,892.77 ኩንታል ምርት እንደ ማስያዣ በመጠቀም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠት ተችሏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በያዝነው በጀት ዓመት 240,809 ኩንታል የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እንደ ማስያዣነት በመጠቀም ከ914,228,000 ብር በላይ በመጋዘን ደረሰኝ ብድር ማቅረብ እንደተቻለ ተገልጿል።
ይህ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አንድ አምራች ወይም ተገበያይ ምርቱን በምርት ገበያው መጋዘን በማስገባት የሚቀበለውን የመረከቢያ ደረሰኝ ብቻ እንደ ማስያዣ በመጠቀም፣ ከምርት ገበያው ጋር በጥምረት ከሚሰሩ ባንኮች ብድር የሚያገኝበት ሥርዓት መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህ አሠራር አምራቾች የፋይናንስ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ምርት ገበያዉ ገልጿል።
በተለይም የቢራ ገብስን መሰሉ አዋጭ የሰብል ዝርያዎች ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓት መግባታቸው አርሶ አደሮች ምርታቸውን በብዛት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር የሚገባውን ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚያስችል ተመላክቷል።@SECO


