የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባደረገው ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ፣ አዲስ አበባን አዲስ ለተቋቋመው የአደጋ እና ሰብአዊ ምላሽ ቢሮ ከዓለማቀፍ 12 ቀጠናዊ ማዕከላት አንዷ አድርጎ መርጧታል።
ይህ በትራምፕ አስተዳደር ይፋ የተደረገው አዋጅ፣ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ በመላው አፍሪካ የሚከናወኑ የአደጋ ጊዜ እርዳታዎችን ለማስተባበር ዋና የክወና ማዕከል እንደምትሆን አረጋግጧል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው ላለፉት 60 ዓመታት የአሜሪካ የዓለማቀፍ እርዳታ ማዕከል የነበረው የአሜሪካ ዓለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) መፍረሱን ተከትሎ የመጣ ነው።
አዲሱ ቢሮ መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ አድርጎ በ200 የሚጠጉ ሰራተኞች የሚመራ ቢሆንም፣ በመሬት ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ግን በአዲስ አበባ፣ ናይሮቢ እና ዳካርን ጨምሮ በ12 የቀጠና ማዕከላት በኩል እንዲከናወኑ ስትራቴጂ ተነድፎለታል።
የቀድሞው ዩኤስኤይድ ሰፊ የልማት ስራዎች ላይ ያተኩር የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ ቢሮ ግን ትኩረቱን በአደጋ እና አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ላይ ብቻ እንዲያደርግ ተወስኗል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደር ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከማህበራዊ ፍትህ ጋር የተያያዙ የረድኤት ፕሮግራሞችን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ፣ በምትኩ በግምት 2 ቢሊዮን ዶላር በተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) በኩል ለሕይወት አድን ተግባራት እንዲውል መድቧል።
ፈጣን ምላሽን ለማረጋገጥ የተቋቋሙት 12ቱ ማዕከላት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ስልታዊ ቦታዎች ተከፋፍለዋል።
በአፍሪካ አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ)፣ ናይሮቢ (ኬንያ) እና ዳካር (ሴኔጋል) ሲመረጡ፣ በአሜሪካ አህጉር ደግሞ ማያሚ፣ ቦጎታ፣ ጓቲማላ ሲቲ እና ሳንቶ ዶሚንጎ ማዕከል ሆነዋል።
በተጨማሪም በዩራሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ ኪየቭ እና አማን፣ እንዲሁም በእስያ ባንኮክ፣ ዳካ እና ማኒላ ተለይተው የአደጋ ጊዜ ምላሽ ስራዎችን እንዲያከናውኑ ተመድበዋል።@SECO


