በኢቢቪ ዘጋቢ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በሀገሪቱ የታየውን አንጻራዊ የዋጋ መረጋጋት ይበልጥ ለማጠናከር የፖሊሲ ወለድ መጠኑ ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑን አስታወቀ።
ባንኩ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ባለፉት ወራት ተግባራዊ የተደረገው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
በተለይም እስከ የካቲት ወር 2018 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ባለው መረጃ፣ ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 9.7 በመቶ ዝቅ ማለቱ የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ የታየበት ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ የምግብ ዋጋ ግሽበት ወደ 10.8 በመቶ፣ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ግሽበት ወደ 8.1 በመቶ መውረዳቸው ለውጤቱ መገኘት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው በሀገሪቱ የታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ካለፉት ስምንት ዓመታት አማካይ የ7.5 በመቶ ዕድገት በልጦ፣ በ2018 በጀት ዓመት 9.2 በመቶ መድረሱን አረጋግጧል።
ለዚህ ዕድገት መመዝገብ የአገልግሎት ዘርፉ በ13.1 በመቶ በማደግ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ በሲሚንቶ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እና በማዕድን ምርት በተለይም በወርቅ ምርት ላይ የታየው ከፍተኛ መነቃቃት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም የግብርናው ዘርፍ የ2.3 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርቱ የራሱን ድርሻ ማበርከቱን ኮሚቴው በዝርዝር ገምግሟል።
የባንክ ዘርፉ በአጠቃላይ ጤናማና በበቂ ካፒታል የተደገፈ መሆኑ ቢገለጽም፣ በአንዳንድ ባንኮች ዘንድ የጥሬ ገንዘብ እጥረት መታየቱን ኮሚቴው ሳይጠቁም አላለፈም።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ ባንክ በባንኮች መካከል ያለውን የገንዘብ ዝውውር ለማሳለጥና የገንዘብ ገበያውን ለማረጋጋት የብድር አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በመንግስት በጀት ረገድም፣ የበጀት ጉድለትን በብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር ከመሸፈን ይልቅ በግምጃ ቤት ሰነዶች ሽያጭ ለመተካት የተሄደበት ርቀት የገንዘብ አቅርቦትን ለመቆጣጠርና ግሽበትን ለመቀነስ ጉልህ ሚና መጫወቱ አስረድቷል።
ምንም እንኳ የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ አመልካቾች አዎንታዊ ቢሆኑም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት በነዳጅ ዋጋና በምርት አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስጋት እንዳለ ተጠቁሟል።
በመሆኑም ብሔራዊ ባንክ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚያስተካክል ገልጾ፣ በቀጣይ በሚያዝያ ወር 2018 ዓ.ም በሚያደርገው ስብሰባ የፖሊሲ እርምጃዎችን በድጋሚ እንደሚመረምር አስታውቋል።@SECO


