የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና የገንዘብ ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ለሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ ከቻይና ባንክ ጋር ከፍተኛ የሥራ ውይይት አካሄዱ።
መጋቢት 23፤ 2018 ዓ.ም የተካሄደው ይህ ውይይት፣ በአህጉሪቱ የአቪዬሽን ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውንና 12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀውን ሜጋ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ያለመ ነው።
ፕሮጀክቱን በበላይነት እያስተባበረ የሚገኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የቻይና ባንክ በጋራ ለመሥራት መነጋገራቸው፣ ለግንባታው የሚፈለገውን ከፍተኛ የፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ታምኖበታል።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ለባንኩ አመራሮች በሰጡት ማብራሪያ፣ ፕሮጀክቱ በቴክኒክ ረገድ ዝግጁ መሆኑንና የፋይናንስ መዋቅሩም በረጅም ጊዜ ዘላቂነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የቻይና ባንክ በበኩሉ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአውሮፕላን ማረፊያ ኢንቨስትመንት ያለውን ተሞክሮ በመጥቀስ በቢሾፍቱ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ “ከፍተኛ ፍላጎት” እንዳለው ገልጿል።
ይህ አዲስ ማረፊያ ተራ የትራንስፖርት ተቋም ብቻ ሳይሆን፣ ሆቴሎችን፣ የገበያ ማዕከላትን እና ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ ፈጣን የባቡር መስመርን ያካተተ “የአውሮፕላን ማረፊያ ከተማ” ሆኖ እንደሚገነባም በውይይቱ ወቅት ተመልክቷል።
የቢሾፍቱ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ በ2030 ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ቀደም ሲል የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር የፈቀደ ሲሆን፣ እስከ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ ሀብት ለማሰባሰብ እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት የቻይና ባንክ ተሳትፎ ለፕሮጀክቱ ስኬት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።@SECO


