የአሜሪካው የማሳቹሴትስ የፌደራል ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ትናንት ባስተላለፈው ውሳኔ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ተጥሎ የነበረው የጊዜያዊ ጥበቃ መብትማብቂያ ጊዜ እንዲራዘም አዘዘ።
ይህ ውሳኔ የሀገሪቱ የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት መብቱን ለማቋረጥ የነበረውን እቅድ ለጊዜው የሚያግድ ነው።
ዳኛ ብራያን ኢ. መርፊ በሰጡት ውሳኔ፣ የጥበቃ መብቱ እንዲቋረጥ የተላለፈው ውሳኔ ሕጋዊ አካሄዱን ያልተከተለ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። በተለይም የሀገር ውስጥ ደህንነት ጸሐፊዋ ክሪስቲ ኖም ውሳኔውን ከማሳለፋቸው በፊት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቂ ምክክር አላደረጉም የሚለው ክስ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል ዳኛው ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ የጥበቃ መብቱ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩ በፍርድ ቤት ታይቶ እስኪያልቅ ድረስ በአሜሪካ የመቆየትና የመሥራት መብታቸው እንደተጠበቀ ይቆያል። ይህም ማለት ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው የማብቂያ ገደብ ምንም ዓይነት ተፈጻሚነት አይኖረውም ማለት ነው።
የኢትዮጵያ የጊዜያዊ ጥበቃ መብት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈቀደው በታህሳስ ወር 2022 ሲሆን፣ በወቅቱ በሀገሪቱ በነበረው ግጭትና ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት ዜጎች ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል በሚል ነበር።
መብቱ በ2024 ተራዝሞ እስከ ታህሳስ 2025 እንዲቆይ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት መብቱን ላለማራዘም ወስኖ እንደነበር ይታወሳል።
አሁን በፍርድ ቤት የተሰጠው ይህ እገዳ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ በሕጋዊ መንገድ መቆየታቸውን እንዲቀጥሉና የሥራ ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።@SECO


