7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመመሥረቻ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ያካሄደ ሲሆን በዋና አፈ ጉባኤነት አቶ አህመድ ሺዴን ሲመርጥ በምክትል አፈጉባኤነት ወ/ሮ አየለች እሸቴን መርጧል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ሆነው የተመረጡት አቶ አህመድ ሺዴ ከጥቅምት 2011 እስከ 2019 ዓ.ም.የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ከመሆናቸው አስቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትርና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አቶ አህመድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ለረጅም አመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በክልል ደረጃ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል ፡፡
አቶ አህመድ ከእንግሊዙ የሱሴክስ ዩኒቨርስቲ ከልማት ጥናት ኢንስቲትዩት በልማት ጥናት፣ አሳታፊነትና በማህበራዊ ለውጥ መስክ የማስተርስ ዲግሪ ከኔዘርላንድስ ሄግ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ጥናት መስክ በገጠር ሃብት አስተዳደርና በሃብት ግጭት አፈታት በማስተርስ ዲግሪ፣ ከእንግሊዙ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ አቶ አህመድ ከኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
በምክትል አፈጉባኤነት ደግሞ ወ/ሮ አየለች እሸቴ የተመረጡ ሲሆን ወሮ አየለች በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚኒስቴር ዴኤታነት እንዲሁም በአማራ ክልል በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃ እንዳገለገሉ ተገልጿል፡፡SECO


