የኢትዮጵያ የቤት ልማት ዕቅድ በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው በቀር ሂደቱን ሊያስተጓጉል የሚችል ትልቅ መዋቅራዊ ችግር እንደገጠመው የዘርፉ ባለሞያዎች አስታወቁ። ይኸውም የሀገሪቱ የባንክ ደንቦች የረጅም ጊዜ የቤት ብድር ፋይናንስን ልዩ ባህሪያት አለማወቃቸው መሆኑን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
እነዚህ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተለመዱት የንግድ ባንክ ደንቦች ከቤት ብድር ገበያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ፈጽሞ እንደማይጣጣሙ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቁጥጥር መመሪያዎች የቤት ብድሮችን ከአጭር ጊዜ የንግድ ብድሮች ጋር በአንድ መልኩ እንደሚመለከቱት ተብራርቷል።
በሁለተኛው የፋይናንስ ፎረም 2026 ላይ የተገኙት የዘርፉ ተዋናዮች እንደገለፁት፣ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ፈጣን የገጠር ወደ ከተማ ንቅናቄ የከተሞች እድገት ወደ 5 በመቶ እንዲደርስ ቢያደርግም፣ የቤት አቅርቦት ጭማሪ ግን ከ0.5 በመቶ በታች አሽቆልቁሏል። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በግምት 5 ሚሊዮን የቤት እጥረት እያጋጠማት ሲሆን፣ በየዓመቱ በአማካይ እስከ ግማሽ ሚሊዮን አዳዲስ ቤቶች ያስፈልጋሉ።
ይህ እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖርም የቤት ፋይናንስ ሴክተሩ በከፍተኛ ሁኔታ መገደቡን ቅዳሜ ገበያ ለመረዳት ችላለች። ባለሞያዎቹ የንግድ ባንኮች ከባድ የጊዜ አለመጣጣም እያጋጠሟቸው መሆኑን ጠቁመዋል፤ ይኸውም በሁለት ዓመት ውስጥ ሊወጡ የሚችሉ የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ገንዘቦችን በመጠቀም የ20 ዓመት የቤት ብድር እንዲሰጡ እየተጠበቁ ይገኛሉ።
የብሔራዊ ባንክ ገዢዉ ከፍተኛ አማካሪ አደራጀዉ ሹመቴ እንዳብራሩት “የራሳችን መመሪያዎችም ብዙውን ጊዜ የረጅም ጊዜ ብድርን ልዩ ባህሪያት የሚያስተጓጉሉ ወይም ግምት ውስጥ የማያስገቡ ናቸው። የሞርጌጅ ብድር የራሱ የሆኑ ልዩ ባህሪያት አሉት፤ መመሪያዎቻችንም እስካሁን ያንን ልዩነት አላወቁትም” ብለዋል።
በእነዚህ የቁጥጥር እንቅፋቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው የቤት ብድር ሽፋን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ከ0.5 በመቶ በታች ሲሆን፣ የወለድ መጠኑ ደግሞ ወደ 18 በመቶ ገደማ ከፍ ያለ እና አግላይ ሆኗል።
ይህን የተገለፀዉ በብሔራዊ ባንክ አዘጋጅነት በተካሄደው ሁለተኛው የፋይናንስ ፎረም 2026 ላይ ሲሆን፣ እነዚህን መዋቅራዊ ክፍተቶች ለማጥበብ መንግስት ቀጣይነት ከሌላቸው አጠቃላይ ድጋፎች እና በቀጥታ በመንግስት ከሚመሩ የግንባታ ሞዴሎች እየራቀ መሆኑ ተገልጿል።
በምትኩ ባለ ሁለት ምሰሶ ማዕቀፍ እየተቋቋመ ይገኛል፤ እነዚህም አቅምን ከግንዛቤ የሚያስገባ ብሔራዊ የቤት ፈንድ እና የገንዘብ እና የጊዜ አለመጣጣም ችግሮችን የሚፈታ ብሔራዊ የሞርጌጅ ሪፋይናንሲንግ ኩባንያ ናቸው።
የሞርጌጅ ሪፋይናንሲንግ ኩባንያ እንደ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ባሉ ስትራቴጂካዊ አጋሮች የሚደገፍ፣ ተቀማጭ ገንዘብ የማይሰበስብ የጅምላ ተቋም ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን የንግድ ባንኮች ነባር የቤት ብድር ንብረቶቻቸውን እንደ ዋስትና እንዲጠቀሙ በመፍቀድ ተቋሙ ለገበያው የረጅም ጊዜ ገንዘብ ያስገባል።
የጎህ ቤቶች ዋና ስራ አስፈፃሚ ግሩም ፀጋዬ በበኩላቸው “በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው ወሳኝ ችግር የረጅም ጊዜ የገንዘብ ፈንድ አለመኖር ነው። ልንፈታው የሚገባን ቁልፍ ጉዳይ ይህ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
1.5 ሚሊዮን ቤቶችን የማድረስ ግብን ማሳካት ከፋይናንስ ባለፈ የተዋሃደ የስነ-ምህዳር አቀራረብን ይጠይቃል።
የቀድሞ የከተማነና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴታ የትምጌታ አስራት ሲናገሩ፤ መንግስት በቀጥታ ከሚያደርገው የግንባታ ሚና ይልቅ የማመቻቸት እና የመደገፍ ስትራቴጂካዊ ሚና ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድሮችን በጥንቃቄ ማፅደቅ እንዲችሉ ለማስቻል መንግስት አዲስ የጸደቀ የሪል እስቴት አዋጅን፣ ደረጃውን የጠበቀ የንብረት ግምገማ ስርዓቶችን እና ቀጣይነት ያለው የካዳስተር እና የባለቤትነት ምዝገባ የዲጂታላይዜሽን ጨምሮ የህግ እና የዲጂታል ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል ተብሏል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በአለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ትብብር 100 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያለው የመጀመሪያው ልዩ የሞርጌጅ ሪፋይናንሲንግ ኩባንያ ለማቋቋም ከስምምነት መደረሱ ይታወቃል።
ተቋሙን ለመደገፍ አይኤፍሲ (IFC) እስከ 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ባንኮችም የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብን ተጠቅመው የረጅም ጊዜ የቤት ብድር በመስጠት ረገድ የሚያጋጥማቸውን የፈሳሽ እና የጊዜ አለመጣጣም ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል።


