ያልተገደበ ኢንተርኔት ማለት ያልተገደበ ፍጥነት ማለት አይደለም ሲሉ የቴሌኮም ባለሙያዎች ገለጹ

 “ያልተገደበ የኢንተርኔት ጥቅል” ማለት በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ያልተገደበ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት ግንኙነት ይኖራል ማለት እንዳልሆነ ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ገለጹ። ባለሙያዎቹ አክለውም፣ በኢትዮጵያ ያሉ ያልተገደበ የኢንተርኔት ጥቅል ተጠቃሚዎች የአገልግሎት ጥራትን አስጠብቆ ለማቆየት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበረውን የፍትሐዊ አጠቃቀም ፖሊሲ በአግባቡ ሊረዱና ሊተገብሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ጉዳዩ በተለይም በኢትዮጵያ ግዙፉ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌኮም ደንበኞች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ወርሃዊ፣ ዓመታዊ እና የተለያዩ የቆይታ ጊዜ ያላቸውን ያልተገደበ የኢንተርኔት ጥቅሎች የገዙ ደንበኞች፣ አገልግሎቱን ከገዙ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ጥሩ ፍጥነት እና ጥራት እንደሚኖረው፣ ሆኖም ጊዜ እየገፋ ሲሄድ የኢንተርኔት ፍጥነቱ እየቀነሰ እና ጥራቱ እየወረደ እንደሚመጣ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተገደበ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት ጥቅል የሚቀርበው በተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ታጅቦ ነው። የቴሌኮም ኩባንያዎች የደንበኞችን ፍላጎት እና ያላቸውን የአውታረ መረብ አቅም ለማመጣጠን ሲሉ የአጠቃቀም ገደቦችን፣ ለመደበኛ ተጠቃሚዎች ቅድሚያ የመስጠት አሠራርን እንዲሁም በፍጥነት ላይ የተመሠረቱ የደንበኝነት ምዝገባ ሞዴሎችን ይተገብራሉ።

የፍትሐዊ አጠቃቀም ፖሊሲ ጥቂት ተጠቃሚዎች ከልክ ያለፈ መረጃ በመጠቀም የሌሎች በርካታ ደንበኞችን የአገልግሎት ተጠቃሚነት እንዳያስተጓጉሉ የሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አሠራር ነው። በጥቅሉ ዓይነት መሠረት፣ አንድ ደንበኛ የተወሰነ የዳታ መጠን ገደብ ላይ ሲደርስ አገልግሎት ሰጪዎች የኢንተርኔት ፍጥነቱን ሊቀንሱበት ወይም አውታረ መረቡ በሚጨናነቅበት ወቅት ለሌሎች ተጠቃሚዎች ቅድሚያ ሊሰጡ ይችላሉ።

ይህ አሠራር በታላላቅ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ዘንድም በስፋት እንደሚተገበር ባለሙያዎች በማስረጃ ያስደግፋሉ። ለአብነት ያህል፣ በአሜሪካ የሚገኘው ቲ-ሞባይል ከፍተኛ የዳታ ፍጆታ ያላቸው ደንበኞች የተቀመጠላቸውን ገደብ ሲያልፉ፣ መስመሩ በሚጨናነቅበት ሰዓት ከሌሎች ደንበኞች ቀጥሎ ቅድሚያ እንዲያገኙ ያደርጋል። ቬራይዘን  በተመሳሳይ የአጠቃቀም ገደቦችን የሚተገብር ሲሆን፣ በእንግሊዝ የሚገኘው ቮዳፎን ደግሞ በአንዳንድ ያልተገደበ ጥቅሎቹ ላይ እስከ 100 ሜጋ ባይት የፍጥነት ጣሪያ ያስቀምጣል። “እነዚህ ዓለም አቀፍ አሠራሮች ‘ያልተገደበ ዳታ’ ማለት በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ያልተገደበ ከፍተኛ ፍጥነት ይኖራል ማለት እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያሉ” ሲሉ ባለሙያዎቹ ያብራራሉ።

የቴሌኮም ተቋማት በርካታ ደንበኞችን በተመጣጣኝ ጥራት የማገልገል ኃላፊነት ያለባቸው የንግድ ተቋማት መሆናቸውን ደንበኞች ሊገነዘቡ ይገባል የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ለዚህም ኃላፊነት የጎደለው የሞባይል ሆትስፖት አጠቃቀምን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ።

አንድ ወርሃዊ ያልተገደበ ጥቅል የገዛ ደንበኛ ኢንተርኔቱን ለአንድ ወይም ለሁለት ሰው ማጋራቱ ብዙም ችግር ባይፈጥርም፣ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ግን ከአምስት በላይ ለሆኑ ሰዎች በማጋራት የዳታ ፍጆታውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲንር ያደርጋሉ።

በተጨማሪም በሌላ ሰው ሆትስፖት የሚጠቀሙ ግለሰቦች ግዙፍ ፋይሎችን እና የሶፍትዌር ማሻሻያዎችን በማውረድ ከዋናው የጥቅሉ ባለቤት በላይ ዳታ ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ይህም በመስመሩ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የዋናውን ተጠቃሚ የኢንተርኔት ፍጥነት እና ጥራት በእጅጉ ይጎዳል። የቴሌኮም ኩባንያዎች እንዲህ ዓይነቱን ያልተለመደ የአጠቃቀም ሁኔታ በኔትወርክ መቆጣጠሪያ ሥርዓቶቻቸው አማካኝነት በቀላሉ መለየት እንደሚችሉ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ባለሙያዎች ለ’ኢቲ ቢዝነስ ቪው’  እንደገለጹት፣ ደንበኞች ጥቅላቸውን በኃላፊነት ሊጠቀሙበት እና በሆትስፖት ለሌሎች ሲያጋሩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ቀኑን ሙሉ ከፍተኛ ዳታ የሚበሉ ፋይሎችን የሚያወርዱ ሰዎችን ከመጋራት መቆጠብ እንደሚገባም መክረዋል።

በደንበኞች ዘንድ ስለ ፍትሐዊ አጠቃቀም ፖሊሲ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ያመኑት ባለሙያዎቹ፣ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የደንበኞቻቸውን ቴክኒካል ግንዛቤ ለማሳደግ ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ምንም ዓይነት ቴክኒካል ብልሽት እስካልተከሰተ እና አገልግሎቱ በኃላፊነት እስከተያዘ ድረስ፣ ደንበኞች በከፈሉበት ጊዜ ሁሉ ቃል የተገባላቸውን የኢንተርኔት ጥራት የማግኘት መብት እንዳላቸውም አጽንኦት ተሰጥቷል።SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ተመረቀ

“ከማገዳችን በፊት ከአምስቴ በላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል!” የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያስመረቀው...

Popular Categories