አዲሱ የጋዜጠኝነት ፋሽን

እውነትን ሳይሆን የፈለኩትን እፅፋለሁ !!

የታዛቢው ሀሳብ

የወቅቱ መንግስት ከቀደመው በተለየ መልኩ የተፈጥሮ ሃብት ለዘርፈ ብዙ የልማት ስራ ቁልፍ ምንጭ መሆኑን በቅጡ ተረድቷል፡፡

ለዚህም ይመስላል ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ለኢትዮጵያ የምድር ውስጥ ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በልማት እቅድ ፖሊስ ውስጥ ጭምር አካቶ እየሰራ የሚኘው፡፡

ያንን በሚደግፍ መልኩ የማእድን ፍለጋ እና ልማት ላይ የተሰማሩ አገር በቀል ሆኑ ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች በመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል ጭምር እየተደረገላቸው ወደ ውጤት እየገቡ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ኩባንያዎች ወደ ምርት እንዲገቡ መንግስት ድርሻ በመውሰድ ጭምር ኩባንያዎችን እየደገፈ ነው፡፡ በተመሳሳይ ግዙፍ የሚባሉ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ኩባንያዎች ሳይቀሩ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ ለመሳተፍ ከከዚህ በፊቱ በተለየ ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡

ለማሳያ የዳንጎቴ ግሩፕ የዘርፉን እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት እንዲሁ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ ግምባር ቀደም የወርቅ ማእድን አልሚዎች መካከል አንዱ የሆነው ዚዥን ጎልድ (Zijin Gold) ኢትዮጵያን ከወርቅ አምራች አገራት ካርታ ሊያካትት የሚችል ግዙፍ የወርቅ ክምችት ያገኘውን አላይድ ጎልድ ኮርፖሬሽንን (Allied Gold) ለመጠቅለል በማቀድ ባለድርሻዎች ድርሻቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመግዛት የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል፡፡

ይህ ዜና ህይወታቸው እና አገራቸው እንድትለወጥ ለሚጓጉ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

መለኪያው ብዙ ነው

ግዙፉ የቻይና የወርቅ ማእድን አልሚ ዚዥን ጎልድ በቀዳሚነት ከሚጠሩ አምራቾች አንዱ መሆኑን ስንጠቅስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ደግሞ ምልከታው ከዛም በላይ ሊሆን ይገባል፡፡

መሰል ትልቅ አልሚ በዘርፉ ቢቆጠር እጅግ አናሳ ከመሆኑ አንጻር ዚዥን መምጣቱ መሰል አቅም ያላቸው አልሚዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ እምነት የሚሰጥ ነው፡፡

በተመሳሳይ ዘርፍ እንኳ ባይሆን ሌሎች ግዙፍ አለም አቀፍ ኩባንያዎች መንግስት ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት መስጠቱን እንዲረዱ መተማመን የሚፈጥር በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚያበረታታ ነው፡፡

በሌላ በኩል መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንደኛው ዋነኛ አላማ ደርዛቸውን የጠበቁ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመመምጣት እራሳቸውን፣ አገር እና ዜጎችን እንዲጠቅሙ አቅዶ እንደመሆኑ ዜናው ለመንግስት ትልቅ እይታ የሚፈጥር ነው፡፡

መለኪያው ብዙ ነው ስንል የቻይናው ኩባንያ በታዋቂዎቹ የኒው ዮርክ እና ቶሮንቶ ስቶክ ኤክስቼንጆች የተመዘገበውን የካናዳው አላይድ ጎለድ ኮርፖሬሽንን ድርሻዎች በሙሉ በመግዛት መጠቅለሉ በራሱ እንደ አገር እና ፕሮጀክት ትልቅ እድል ነው፡፡

በዚህ ደረጃ በሁለቱ ግዙፍ የፋይናንስ ገበያ ውስጥ የተመዘገበውን አላይድ ጎልድ የመጠቅለል እድል ያገኘው ዚዥን ጎልድ ባለድርሻዎችን ወይም የካናዳውን ኩባንያ አመራሮች ለማሳመን የሚያስችል የገንዘብ አቅም እንዳለው አመላካች ነው፡፡

በመሆኑም አላይድ ጎልድ ይዞት የነበረውን ኩምሩክ የወርቅ ማእድን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት ትልቅ እድል የፈጠረ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ አካባቢ የሚገኘውን ከፍተኛ የወርቅ ክምችት በፍለጋ ያገኘው አላይድ ጎልድ ወደ ልማት ለመግባት አታካች የሚያሰኙ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ወደ ምርት ለመግባት እንቅስቃሴ እያደረገ የነበረ ኩባንያ ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ የዚዥን ጎልድ ወደ መድረኩ መምጣት ለካናዳው ኩባንያ ባለድርሻዎች ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብስራት መሆኑ ዘርፉን በቅጡ ለሚረዱ አካላት እና ባለሞያዎች ግልፅ ነው፡፡

የሁኔታው አቀባበል

ዚዥን ጎልድ አላይድ ጎልድን ሊጠቀልል ነው የሚለው ዜና በኩባንያዎች ይፋ የተደረገው ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ጥር 19 ቀን 2018 መሆኑ ይታወሳል፡፡

መረጃው ከወጣ በኋላ በርካታ አገር በቀል ሆነ ስመ ጥር አለምአቀፍ ሚዲያዎች ይህን ግዙፍ የሽያጭ ዜና ሽፋን ሰጥተውት አስተውለናል፡፡

በርግጥ በእስያ በቀዳሚነት ከሚጠሩት አንዱ በሆነው የሆንግ ኮንግ አክሲዎን ገበያ የተመዘገበው ዚዥን ጎልድ በሰሜን አሜሪካ የተሟሟቁ በሚባሉት ኒው ዮርክ እና ቶሮንቶ አክሲዎን ገበያዎች ድርሻ ለመሸጥ የተመዘገበውን አላይድ ጎልድን ጠቅልሎ መግዛቱ ትልቅ ዜና መሆኑ የሚደንቅ አይሆንም፡፡

የግብይት መጠኑም እንዲሁ ከፍ ያለ ነው፡፡

የቻይናው የወርቅ ኩባንያ ውሉ ሲጠናቀቅ ከ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ወዲያው ለመክፈል ነው የተስማማው፡፡ ይህ ነው ግዙፉ ድርጅት ኢትዮጵያ በጉጉት ወደምትፈልገው የማአድን ልማት ለመምጣቱ አንደኛው ማሳያ፡፡

እንዲያም ሆኖ በተለይ አንዳንድ የአገር ውስጥ እና መሰረታቸውን ውጭ ያደረጉ በኢትዮጵያ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ሚዲያዎች የትኩረት አቅጣጫ እና የዜና አዘጋገብ መርህ ትዝብት ላይ የሚጥል ሆኖ ነው ያገኘነው።

ልውጥ እይታ እና ትኩረት ፍለጋ

ስለሚዲያ በቂ ግንዛቤ ያለው ሰው የሚሰራው ዜና ቀና ወይም እሱን የሚመለከት ይሁን አይሁን የሚዲያዎችን ትኩረት መረዳት ይጠበቅበታል፡፡

እንደሚታወቀው ሚዲያዎች የህዝብ ወገን ሆነው ለዜጋ እና አገር የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ማገዝ አይነተኛ ተግባራቸው ነው፡፡ ዜጋን ወይም ስለሆነ ጉዳይ መረጃ ለሚፈልግ ሰው (የውጭ ሰውም ሊሆን ይችላል) መረጃ ማቀበል ከሚዲያዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

እውቀት አጠር ዘገባ እና ዘርፉ የሚጠይቀውን የሞያ መርሆች የሳተ ዘገባ ግን ለዘርፉ እጅግ አደገኛ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በተለየ የፖለቲካ ፍላጎት መንግስትን ወይም ስልጣን ላይ ያለን አካል ለመጉዳት አልሞ መንቀሳቀስ፣ እኔ ያልበላሁት ለሌላ አይሆንም የሚል አጥፊነት፣ የግል ፍላጎት ወይም ጸብ፣ እኔ ነኝ ሰውየው የሚል የበታችነት እሳቤ፣ ቆይ እሰራልሃለው የሚል ደባ፣ ወይም ይህን ካላረክልኝ ስምህን አጠፋለሁ የሚል የሌብነት አስተሳሰብ ግን ለሚዲያው፣ ሚዲያውን ለሚመራው ወይም ለጋዜጠኛው ጨርሶ የሚሰራ አይደለም፡፡

በዚዥን ጎልድ እና አላይድ ጎልድ መካከል የድርሻ ሽያጭ ስምምነት ተደረሰ መሰኘቱን ተከትሎ ያስተዋልናቸው አንዳንድ ዘገባዎች በአገር፣ ህዝብ እና መንግስት ላይ ጉዳትን ለማስከተል ያለሙ ከመምሰል በዘለለ የጋዜጠኝነት ዘርፉ በአደገኛ ቅኝት እየዳከረ ለመሆኑ ጥሩ አመላከች ናቸው ለማለት ያስደፍራል።

ቀደም ሲል እንደተገለፀው አላይድ ጎልድን የቻይና ኩባንያ ሊጠቀልለው ነው የሚለው መረጃ በኩባንዎቹ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ግብይቱ ትኩረት በመሳቡ ትልልቅ አለም አቀፍ የዜና አውታሮች እንዲሁም በአገር ውስጥ ስመ ጥር የሆኑ የግል ሚድያዎችን ጨምሮ ዜናውን ሽፋን ሰጥተውታል።

በአንጻሩ ከጀርባ ምን አለ የሚሉ የተለየ እይታ ጉዳዩ ይፈልጋል ብለው ዘገባ ያወጡ እና ያራገቡ አሉ፡፡

እውነት ለመናገር የሚዲያ ዋናኛ ስራ ከጀርባ ያለውን አነፍንፎ ለህዝብም ሆነ ለሚመለከተው ማጋራት ዋነኛ ተግባር መሆኑን ስለሚዲያ ምንነት የሚረዳ ሰው አይስተውም፡፡ ቅሬታ ሊያድርበትም አይገባም፡፡

እንዲያም ሆኖ ባለፈው ሳምንት በአላይድ ጎልድ እና ዚዥን መካከል የተደረገውን ግብይት ተከትሎ ከጀርባ ሌላ ነገር አለ የተባለበትን ዘገባ ለመስራት የጣሩ የሚዲያ ተቋማት እና ጋዜጠኞች ድብቅ ያሉትን መረጃ ማውጣት የመሰላቸው፦

1. የማያቁትን እና በጭራሽ ያልሆነ ነገር እውነት በማስመሰል ህዝብ ማደናገር፡፡

2. የጋዜጠኝነት ሆነ የዜና ዘገባ መርህን የረሳ እና የዘርፉን ባለሞያዎች በእጅጉ ያዋረደ አካሄድ በመከተል የራስን ሃሳብ “ምንጮቼ ነገሩኝ እና የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት” በሚል ሰበብ የውሸት ዘገባን በሌሎች ጭምር የተመሰከረ እውነት ለማስመሰል መሞከር፡፡

3. የነበረ እና ያለ እውነትን መጠቀም ሲቻል ያንን በመሸሸግ ከጀርባ ሌላ ነገር አለ ለማስባል ጥረት ማድረግ፣ እና የመሳሰሉትን  መከወን ነው።

በርግጥ ሚዲያን በደንብ ለሚረዳ ሰው አንዳንዶች የግል ፍላጎታቸውን ምንጭ ነገረኝ፣ ሰነዶች ይሄን ይላሉ፣ እና እንዲ ሊሆን እንደሚችል ባለሞያዎች ይናገራሉ በሚል ጭምር በዘገባ ስም ልክ ልኩን ነገርኩት አይነት እንደሚሰሩ ከወርቅ ኩባንያዎቹ ግብይት ጋር ተያይዞ የተሰሩ ዜና መሰል ዘገባዎች ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡

እጅግ አስፈሪው ነገር ደግሞ እንትና የሚባል ኩባንያ ተመሳሳይ ነገር ስለሰራ ይሄኛውም እንደዛ ማድረጉ አይቀርም የሚል የቢሆን አመክንዮ ዜናን በሚያክል ሁለት ሶስት ጊዜ እውነታ መጣራት በሚፈልግ የጋዜጠኝነት ዋነኛ ንኡስ መስክ መመልከታችን ነው፡፡

ሚዲያ በባህሪው አንዱ ቀድሞ ያገኘውን ሌላኛው ተቀብሎ መዘገብ የተለመደ ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ ቀድሞ መረጃውን ይፋ ላደረገው እውቅና መስጠት ተገቢ እንደመሆኑ ሁሉ እንትና የተባለ ጋዜጠኛ ወይም አክቲቪስት በገጹ ያጋራውን መረጃ በምንጮቼ ነገሩኝ ሰበብ ምንም ተጨማሪ የማጣራት ስራ ሳይሰሩ እና እውቅና ሳይሰጡ እንዲያው ዝም ብሎ እውነት አስመስሎ ሲዘግቡ መመልከት እጅግ ያስደነግጣል፡፡

መሰረታዊ የሚዲያ ህግጋትን የሳተ ወሬ ማራገብ እራሳቸውን ትልቅ እንደሆኑ ከሚናገሩ የአገር ውስጥ ሆነ የውጭ ተቀማጭ የኢትዮጵያ ሚዲያ ተቋማት እና አንጋፋ ጋዜጠኞች መመልከት ዘርፉ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደገባ አመላካች ነው፡፡

እውነት እና እውቀት

ላገር ከጠቀመ የሁለቱ ኩባንያዎች ግብይትን ተንተርሶ የተሰሩ አዎንታዊ ዜናዎች መሰራታቸው ተገቢ መሆኑ የማያደራድር ሃቅ ነው፡፡

በጣት የሚቆጠሩ ሚዲያዎች እውነት አለን፣ ምንጮቼ ነገሩኝ፣ ባለሞያዎች እንደሚሉት ወይም መሆኑ አይቀርም የሚል መላ ምት ሁሉ ጨምረው በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ እውነታው ይህ ነው የሚል በተለይ አላይድ ጎልድን ክፉኛ ወርፈው ጭምር ዜና ሰርተው ታይተዋል፡፡

እጅግ ተፋልሶ የተመለከትነው የጋዜጠኝነት መርህን እንተው እና ንጽጽራዊ እውቀት እና እውነት ላይ ትኩረት እናድርግ፡፡

ዜና ዘጋቢ ስለሚሰራው ሁሉ የቀደመ እውቀት ቢኖረው አይባልም፡፡ ይሁን እንጂ ጋዜጠኝነት በተለይ ለዜና ባለሞያ መሰረታዊ እውቀት እና የሚነገረውን ሆነ የሚያነበውን መረዳት ወይም ለመረዳት አቅም መፍጠር የሞያው ሀሁ ነው፡፡

መረዳት ካዳገተ ግን አንባቢ ወይ ሰሚ መሳሳቱ ነው እና፤ የተገኘን መረጃ ዝም ብሎ ከማሰራጨት መቆጠብ የግድ ነው፡፡

ለምሳሌ በአፍሪካ ማሊ፣ ኮትዲቯርና እና ኢትዮጵያ የወርቅ ፍለጋ እና ልማት ላይ የተሰማራው አላይድ ጎልድ እና ግዙፉ ቻይናዊ የማእድን አልሚ ለሽያጭ የተስማሙት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩምሩክ ለሚገኘው የአላይድ ወርቅ ፕሮጀክት ሳይሆን በኒው ዮርክ እና ቶሮንቶ ስቶክ ገበያዎች ተመዝግቦ የሚገኘውን አላይድ ጎልድን ለመጠቅለል ነው፡፡

በቅርቡ በወጡ ዘገባዎች ይሄን እውነታ ባለማወቅም ሆነ ሆን ተብሎ ተሳስቶ ቀርቦ ተመልክተናል፡፡

በኩባንያዎቹ ስምምነት መሰረት አላይድ የያዘውን ድርሻ በጠቅላላ የቻይናው ዚዢን ጎልድ ይዞ አላይድ ጎልድ በስሩ የሚገኝ አንድ ንዑስ ድርጅት (Subsidiary) ሆኖ ይቀጥላል፡፡

እዚህ ላይ ከጀርባ ያለውን እናውጣ ያሉ ሚዲያዎች በእውቀት ወይም ጊዜ እጥረት የዘለሉት እና መጠቀስ ያለበት ሃቅ ቢኖር ኩምሩክ ወርቅ ማእድን በኢትዮጵያ ህግ የተመሰረተ የወርቅ ፍለጋ እና አልሚ ኩባንያ ነው፡፡

ኩባንያው አስኮም ማይኒንግ ኢትዮጵያ በተሰኘ የግብጽ እና ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዎኖች ተመስርቶ የነበረ ቢሆንም እኤአ በ2017 ገሚሱን እንዲሁም 2023 ሙሉ በሙሉ በተደረሰ ውል የግብፅ ባለሃብቶች ያላቸውን ድርሻ ለአላይድ ጎልድ በመሸጥ ከኩባንያው ሙሉ ለሙሉ  ወጥተዋል፡፡

ይህም ማለት ኩባንያው የግብፅ ባለድርሻዎች የሌሉት፤ ድርሻቸውንም በ2023 ለቀው ሲወጡ ሁለቱ ወገኖች ያከፋፈል ሰምምነት ያላቸው እና ያም በውሉ መሰረት ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡

እኚህ ጥቂት ዘገባዎች በአስኮም እና አላይድ መካከል የዘለቀ የጥቅም ግንኙነት እንደሚኖር አዋቂ ለመምሰል በሚመስል መልኩ ሌላ የቁጥር ስሌት እና የቀጠለ ክፍያ እንዳለ በቂ ማስረጃ ሳያቀርቡ ዜና ሰርተዋል፡፡

አለያ አላይድ የመክፈል አቅም እንደሌለው ምንም አይነት የተነሱበትን ሃሳብ የሚደግፍ ማረጋገጫ ሳይሰጥ መለጠፍ ከኩባንያ አሰራር እውቀት ጋር የተጣላ ጋዜጠኝነት ስለመኖሩ ዘገባዎቹ አመላካች ናቸው።

ልክ ልኩን ነገርኩት የሚል የራስ እና ጥቅም ተጋሪ የሆኑትን ከማስደሰት ያለፈ አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡

እውነታው ተጣርቶ የጉዳዩ ባለቤት ተጠይቆ ቢዘገብ የሚያሰኘው ነገር ደግሞ በስማ በለው አሉ አሉ የተባሉ ሚዲያዎች እና ጀሌዎች የወረወሩት ሌላው ጉዳይ የግብጽ የወታደር ተቋም ከሰሞኑ የወርቅ ኩባንያ ግብይት የጥቅም ተጋሪ ተደርጎ መሳሉ ነው፡፡

በመሰረቱ ዜና ሰራን የሚሉ ሚዲያዎች ሆኑ ጋዜጠኞች ስለ አክሲዎን ገበያ መሰረታዊ የሚባሉ መርሆዎች አንዳች እውቀት ወይም የማወቅ ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹበት የዜና ዘገባ ጉዳዩን ለሚረዱ ተንቆ እንዲተው ምክንያት ይሆናል፡፡

የግብፅ ሆነ የህንድ አለያ የቻይና ብቻ አቅም ያለው በግዙፍ የስቶክ ገበያዎች መሳተፍ የሚችል ግለሰብ ይሁን ኩባንያ አይደለም በኢትዮጵያ በመላው አለም የሚገኙ ቢዝነሶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ጥቅም ተጋሪ ሊሆን መብት አለው እየተሰራበትም ነው፡፡

አይደለም ኒው ዮር ወይም ሆንክ ኮንግ የሚገኝ የስቶክ ኤክስቼንጅ፤ ጀማሪ ቢሆን እንኳ የአክሲዎን ገበያ ማእከል ጠንካራ መሰረቱ፡

 -ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት መሆኑ፣

-እያንዳንዱ ስቶክ ላይ ያለ ኩባንያ እንቅስቃሴ በቅፅበት ለህዝብ ይፋ የሚደረግበት መሆኑ፣

-ሃቀኝነቱ እና የጠራ አካሄድ ማንገቡ ነው፡፡

ይህን ለሚረዳ ሰው ይልቁንም መረጃ ፈልፍሎ ለህዝብ ላቅርብ ለሚል የተከበረ ጋዜጠኛ በህዝብ መድረክ ባደባባይ አክሲዎኑ እና ባለአክሲዎኖቹ ስለተመዘገቡለት ኩባንያ ያን ያህል የተሳሳተ መረጃ ማጋራት ለዕውቀት ቦታ ያለመስጠት እና አንባቢን የመናቅ ካልሆነ ምን ይባላል!

ለመድገም ያክል የስቶክ ገበያ የአሰራር መርሆዎችን እና ጠንካራ የቁጥጥር፣ አስገዳጅ የግልፀኝነት እና የህግ ትግበራን የማይረዱ እገሌ ይህን ያህል አክሲሆን አለው ከአዲሱ ሽያጭ ይሄን ያህል ኮሚሽን ያገኛል ማለት በአላዋቂዎች እና በኢትዮጵያ ጠላቶች ዘንድ ዝናን ያስገኝ ካልሆነ በስተቀር የተዛባ መረጃ በማቅረብ አገር እና ህዝብ ይጠቀማል ማለት ዘበት ነው፡፡

ሞያዊ እውቀት አጠር ብሎም አንባቢ እና አድማጭን የናቀ የስነምግባር ጥሰት ከሰሞኑ አሉታዊ ዘገባ መረዳት የሚቻልበት ሌላኛው አካሄድ የዛሬ ስንት አመት እገሌ የተሰኘ ኩባንያ እንዲ አድርጎ፣ እንዲህ ሰርቶ ስለነበር ይሄኛውም ኩባንያ ይህን ሊያደርግ ይችላል የሚል መላ ምት በዜና ዘገባ ለዚያውም ስማቸው ከገዘፉ ተቋማት መመልከት የኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንደስትሪ እኛ ሳንሰማ ፋሽኑን ቀየረ እንዴ ያሰኛል፡፡

ሌላው ቢቀር ይሄ ኩባንያ ምርት በዚህ ጊዜ እጀምራለው ብሏል፤ ሸጦ ሲወጣ በተባለው ጊዜ ምርት እንደሚጀምር ቆይ እናያለን!! ተብሎ ዜና ላይ ዛቻ መሰል ሃሳብ ሲቀርብ ኤዲተር እንዴት ይሄን ዜና ያሳልፋ ያሰኛል።

ወይስ እኛም ከሰሞኑ እንዳየነው የዘገባ ስታይል፣ “ዜናው ለአገር ወሳኝ እንደሆነ የሚጠበቅ የወርቅ ልማት ጉዳይ ነው ወይስ የግል ባህሪን ማሳያ፣” ነው ሲሉ አንዳንድ የዘርፉ ባለሞያዎች ጠይቀዋል ብለን እንተወው፡፡

እንዲያም ሆኖ የአላይድ እና ዚዥን የሽያጭ ስምምነት ያበሳጫቸው የህዝብን እና አገር ጥቅም የሚመቀኙ አካላት መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ቁልፉ ጥያቄ መሆን ያለበት የጋዜጠኝነት በተለይ ምሰሶ የሆነው የዜና ዘገባ ሞያ እንዲህ የግል ፍላጎት ማንፀባረቂያ ሆኗል የሚለው ነው፡፡

ኩምሩክ ወርቅን የሚያክል ግዙፍ እና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የልማት አቅጣጫ ለመምራት የበኩሉን ወሳኝ ሚና የሚጫወት ፕሮጀክት እጅግ ከፍ ያለ አቅም ባለው ኩባንያ መያዙ ብቻ ሳይሆን የኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ መግባት ብቻውን ሌሎች በርካታ ኩባንያዎችን የሚስብ መሆኑን በቧለሞያ አስተያየት ማዳበር ነው የሚሻለው ወይስ አላይድ ይሄን የመሰለ ግዙፍ እና ተስፋ ያለው ፕሮጀክት በዚህ ወሳኝ ምእራፍ መሸጡ አሳማኝ አይደለም ሲሉ ባለሞያዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው ብሎ ዘገባ መስራት።

በዚህ ሰአት እንዴት ይሸጣሉ ብሎ መጥቀስ ለሻጮች በማዘን ነው ወይስ የግል ፍላጎት? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጉ አይቀርም፡፡

ኢትዮጵያ ገና ብዙ እውነትን ፈልፍለው የሚዘግቡ፣ የህዝብ እና የሀገር ጥቅምን ዋና ጉዳያቸው አድርገው የሚሰሩ ሚድያዎችና ጋዜጠኞች ትፈልጋለች፡፡

እንዲህ፣ ከላይ እንዳነሳነው አይነት ጋዜጠኝነት ግን የህዝብ ፍላጎት ሌላ “የጋዜጠኛው” መንገድ ሌላ ያስብላል፡፡ኝነት ግን የህዝብ ፍላጎት ሌላ “የጋዜጠኛው” መንገድ ሌላ ያስብላል፡፡@SECO

Related

When Investigative Journalism Becomes Advocacy: Questions Raised by Middle East Eye’s Kurmuk Gold Mine Report

By Yehenalem Wondu Investigative journalism has an important role to...

When the Internet Gives You a Joke, Use It

A word that was supposed to be a punchline...

ከ9 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃት ተሞክሯል

የኢትዮ ቴሎኮም  ቺፍ ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ እንዳለ አስራት እንደገለጹት...

Experts Urge Debt Service Caps to Solve Africa’s Water Crisis

“The African Union should be more than an annual...

Popular Categories