የሸበሌ ባንክ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማስፋፋት የጀመረውን ስልታዊ ጉዞ ተከትሎ፣ በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ባንኮች ከባንኩ ጋር አብሮ ለመስራት እና አክሲዮኖችን ለመግዛት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑ ተገለጸ።
ባንኩ ከጁቡቲ በመቀጠል በኬንያ ከሚገኙ የቢዝነስ መሪዎች ጋር ባካሄደው ሁለተኛው የውይይት መድረክ ላይ እንደተመለከተው፣ የባንኩ ቀጠናዊ ተጽዕኖ እያደገ መጥቷል።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በኬንያ የኢትዮጵያ አአምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ፣ የጋሪሳ እና የኢሲዮሎ ግዛት አመራሮች እንዲሁም ታዋቂ የንግድ ሰዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በባንኩ የወደፊት ራዕይ ላይ ያላቸውን እምነት ለመግለጽ የአክሲዮን ግዢ የፈጸሙ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ተቀባይነት የሚያጠናክር ሆኖ ተገኝቷል።
በባንኩ እንደገለፁት ፣ ለዚህ ከፍተኛ የባለሀብቶች ፍላጎት ዋነኛ ምክንያቶች ባለፉት ጥቂት ወራት ባንኩ ያስመዘገበው ጠንካራ የፋይናንስ አፈጻጸም፣ በኢትዮጵያ በቅርቡ የተተገበሩት ማይክሮ-ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች፣ በተለይም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር መመሪያ መውጣት፣ የቀጠናው ምቹ የንግድ ሁኔታ እና የባንኩ ስልታዊ ዕቅድ መሆናቸው ተጠቅሰዋል።@SECO


