የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ዘንድ የሚታየውን የዜሮ፣ የኪሳራ እና የክሬዲት ሪፖርት አቀራረብ መጨመር ለመግታት የሚያስችል “የግብር ተገዢነት ማሻሻያ እቅድ” የተሰኘ አዲስ ስልታዊ ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑ ታወቀ።
ካፒታል ጋዜጣ እንደዘገበው፣ ይህ እቅድ የግብር ስወራ ስጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና የግብር ክፍያ አፈጻጸምን ለማሻሻል ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዋናነት የግብር ፋይሊንግ ቁጥጥርን ማጥበቅን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ አሰራርን ማጠናከርን እና ግዴታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰድን ያካትታል።
እስከ ሰኔ 2026 ተጠናቆ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ እቅድ፣ ታህሳስ 2026 ድረስ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ ለዚህም ስኬታማነት ሚኒስቴሩ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ነባሩን የሲግታስ ሶፍትዌር የሚተካና የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ አጠቃቀምን የሚያሰፋ አዲስ የቴክኖሎጂ ስርዓት በመገንባት ላይ ይገኛል።
ይህ እርምጃ የመንግስትን የመካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂ ግቦችን ለማሳካትና በተለይም ትርፍ እያገኙ ኪሳራ ሪፖርት የሚያደርጉ ተቋማትን ተጠያቂ በማድረግ የታክስ ስርዓቱን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።@SECO


