በኢቢቪ ዘጋቢ
የኢትዮጵያን የቆዳ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና ዘርፉ ያለበትን የአካባቢ ጥበቃ ተገዢነት ችግር ለመፍታት በሞጆ ከተማ የጋራ የቆሻሻ ማከሚያ ሥርዓት ያለው ‘ሌዘር ሲቲ’ እየተገነባ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስትር የዉጪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን አበበ እንደገለጹት፣ የቆዳ ኢንዱስትሪው በአሁኑ ወቅት ካለበት ማነቆ ወጥቶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶችን ማሟላት ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።
“የቆዳ ፋብሪካዎች በባህሪያቸው ከፍተኛ ፈሳሽ ቆሻሻ የሚያመነጩ በመሆናቸው፣ ይህንን በዘመናዊ መንገድ የሚያክም ሥርዓት መዘርጋት ለዘርፉ ህልውና ወሳኝ ነው” ብለዋል።
ይህ የተነገረው፤ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኀበር ለ15ኛ ጊዜ የሚያካሂደውን የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርዒት ሜሴ ፍራንክፈርት ከሚባል መሰረቱን ጀርመን ሀገር ካደረገ አለም አቀፍ ንግድ ትርዒት አዘጋጅ ጋር በጋራ ለማከናወን ከስምምነት ላይ መድረሳቸው በተገለፀበት ወቅት ነዉ።
በግንባታ ላይ ያለው ይሄው ‘ሞጆ ሌዘር ሲቲ’ ፋብሪካዎችን በአንድ ፕላትፎርም በማሰባሰብ የጋራ የቆሻሻ ማከሚያ ፕላንት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው። ይህም ፋብሪካዎች በተናጠል ለቆሻሻ ማከሚያ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ፣ ምርቶቻቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት እንዲያገኙ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለጻ፣ ኢንዱስትሪዎቹ ይህንን ዓለም አቀፍ የአከባቢ ጥበቃ ደረጃ ማሟላት ሲችሉ የገበያ ተወዳዳሪነታቸው ይጨምራል። ይህም ወደ ውጭ የሚወጣውን ጥሬ ቆዳ በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ዋጋ ተወዳድረው የመግዛት አቅማቸውን የሚያሳድገው ሲሆን፣ የቆዳ ግብዓት እጥረቱንም በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል።
ይህ የ’ሞጆ ሌዘር ሲቲ’ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የቆዳ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።@SECO


