በኢቢቪ ዘጋቢ
የማዕድን ሚኒስቴር የምርመራ ሂደታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ምዕራፍ ለሚሸጋገሩ ሦስት ግዙፍ ኩባንያዎች የምርት ፈቃድ ሰጠ።
ኩባንያዎቹ በአጠቃላይ ከ4.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸው በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በስምምነቱ መሠረት የብረት ማዕድን ምርት ፈቃድ የተሰጠው ለዜድ ዋይ ቲቢ-ዲ ኤይ ኤም ስቲል ማኑፋክቸሪንግ (ZYTB-DAM Steel Manufacturing) ኃላ/የተ/የግል/ማህበር ነው። ኩባንያው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የፋብሪካ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ምርት ሥራ በመግባት የሀገሪቱን የብረት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራ ታውቋል።
በተመሳሳይ በወርቅ ምርት ዘርፍ የተሰማራው ቤሮ ማይኒንግ ኤንድ ትሬዲንግ (Bero Mining and Trading) ኃላ/የተ/የግ/ማህበር የምርት ፈቃድ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህ ኩባንያም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ ምርት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
በዕለቱ ከተከናወኑት ዋና ዋና ኩነቶች መካከል ሌላው ስልታዊ ስምምነት፤ በማዕድን ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) መካከል የተደረገው የፖታሽ ማዕድን ልማት ስምምነት ነው። ስምምነቱን የሆልዲንግሱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ እና የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኔ ፈርመዋል።

ይህ ትብብር ለዘመናት ሳይለማ የቆየውን ሰፊ የፖታሽ ክምችት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ እና የግብርና አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው።
ዶ/ር ብሩክ ታዬ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ያላትን የፖታሽ ሀብት ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብና ለማዳበሪያ ምርት ግብዓትነት ለመጠቀም ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በተለይም ማዕድኑን አጥሮ ከመያዝ ይልቅ በአግባቡ ወደ ስራ የሚያስገቡ ኩባንያዎች ላይ ትኩረት ለሚያደርገው አዲሱ ስትራቴጂ EIH ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወት አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኔ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ግዙፍ ከሆነው የሉዓላዊ ሀብት ፈንድ (EIH) ጋር አብሮ መስራት የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ ስልታዊ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህ ትብብር የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በኃላፊነት ስሜት በማልማት ለረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት ለመጣል ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከማሳደግ ባለፈ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያመጡም ታምኖባቸዋል።@SECO

