የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚገኘውን ቋሚ ቢሮውን መልሶ ለመክፈት የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩ ታውቋል።
በልዩ መልዕክተኛው መሐመድ በላኢሽ የተመራ የህብረቱ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን ያቀና ሲሆን፣ ዓላማውም በዋና ከተማዋ ያለውን የጸጥታና የመሠረተ ልማት ሁኔታ በመገምገም ቢሮውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ከሦስት ዓመታት በኋላ ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ከፖርት ሱዳን ወደ ካርቱም መመለስ በጀመሩ ማግስት ነው።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሂዲን ሳሌም የልዑካን ቡድኑን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፣ መንግሥት ካርቱምን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ለመመለስ እያከናወነ ስላለው ተግባር ገለጻ አድርገዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ከመጋቢት 2025 ጀምሮ የሀገሪቱ ጦር በዋና ከተማዋ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ካገኘ በኋላ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች እንዲመለሱ ተደርጓል።
ይህም በርካታ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲነቃቁ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ መሐመድ በላኢሽ በበኩላቸው፣ ጉብኝቱ ህብረቱ በሱዳን ያለውን ዲፕሎማሲያዊ መገኘት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ልዑካን ቡድኑ በካርቱም ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መገምገሙ ለቢሮው ደህንነቱ የተጠበቀ አሠራር ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ልዩ መልዕክተኛው፣ የሱዳን መንግሥት ለሚያደርገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ህብረት ቢሮውን በካርቱም መልሶ ለመክፈት ለሚያደርገው ጥረት ማንኛውንም አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።@SECO


