በኢትዮጵያ የሚገኙ መድህን ሰጪ (ኢንሹራንስ) ኩባንያዎች ወቅቱ ለሚጠይቀው የዲጂታል ሽግግር ዝግጁ ባለመሆናቸው፣ አዲስ ወደ ዘርፉ እየገቡ ባሉ የቴክኖሎጂ ተቋማት (InsurTech) የመዋጥ አደጋ እንደተደቀነባቸው በቅርቡ የወጣ ጥናት አመለከተ።
የኢትዮጵያ መድህን ሰጪዎች ማህበር ፕሬዝዳንትና የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ያሬድ ሞላ ባቀረቡት ጥናታዊ ሪፖርት መሠረት፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አሁንም በወረቀትና በእጅ በሚከናወኑ አሰልቺ ስራዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ስጋት ሆኗል።
ደንበኞች በባንክ ዘርፍ የለመዱትን ፈጣንና በሞባይል የታገዘ አገልግሎት ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች በማጣታቸው፣ ወደ ተሻሉ አማራጮች የመሄድ ዝንባሌ እያሳዩ መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል።
የዘርፉ መዘግየት ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው ከተለዩት መካከል የአመራሮች ለቴክኖሎጂ ያላቸው ዝቅተኛ ትኩረት፣ ግልጽ የሆነ የዲጂታል ስትራቴጂ አለመኖርና የቁጥጥር ስርአቱ ለለውጥ የሚያደርገው ግፊት አናሳ መሆን ተጠቃሾች ናቸው ሲል የዘገበው ካፒታል ጋዜጣ ነዉ።
ዓለም አቀፉ የኢንሹራንስ ገበያ እንደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለፖሊሲ ሽያጭና ለካሳ ክፍያ እየተጠቀመ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከነባራዊው አሰራር ካልወጡ የረጅም ጊዜ ህልውናቸውን ማረጋገጥ እንደማይችሉ አቶ ያሬድ አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም ኩባንያዎች ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት፣ በቂ በጀት በመመደብና አሰራራቸውን በማዘመን ደንበኞቻቸውን ሊታደጉ እንደሚገባ ጥናቱ በአጽንኦት ማሳሰቢያ መስጠቱን ዘገባው አመልክቷል።@seco


