የአፍሪካ ልማት ባንክ (AfDB) በኢትዮጵያ ለሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ገለልተኛ የአበዳሪዎች ኢንሹራንስ አማካሪ ለመቅጠር የፍላጎት መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሚገነባው ይህ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የአህጉሪቱ ትልቁ የአቪዬሽን ማዕከል እንዲሆን ታቅዶ የተነደፈ መሆኑን ባንኩ ጠቁሟል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ እንደ ዋና አበዳሪ አስተባባሪ በመሆን ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር የብድር ሂደቱን የሚያከናውን ሲሆን፣ ተመራጩ አማካሪ ድርጅት በፕሮጀክቱ ኢንሹራንስ መስፈርቶች፣ ሰነዶችና ክትትል ላይ ገለልተኛ ግምገማ የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል ብሏል።
አማካሪው በቀጥታ ሪፖርት የሚያደርገው ለባንኩ ቢሆንም፣ በብድር ሂደቱ ለሚሳተፉ ሁሉም አበዳሪዎች ተገቢውን የጥንቃቄ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት።
ባንኩ ብቃት ያላቸውን የአማካሪ ድርጅቶች የፍላጎት መግለጫ (EoI) እንዲያቀርቡ የጋበዘ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ ያላቸውን የባለሙያ ብቃት፣ ተመሳሳይ ስራዎችን የመስራት ልምድና ከዓለም አቀፍ የልማት ባንኮች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።@seco


