የኬንያ መንግሥት በ2026 የፋይናንስ ረቂቅ አዋጅ አማካኝነት የክሪፕቶ ምንዛሬ ልውውጥ የሚያደርጉ ተቋማት የደንበኞቻቸውን ማንነትና የግብይት መዝገቦችን ለታክስ ባለሥልጣናት ይፋ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ አዲስ ሕግ አቀረበ።
ይህ አዲሱ ሕግ የኬንያ ገቢዎች ባለሥልጣን የክሪፕቶ ግብይቶችን፣ የሚገኘውን ትርፍ እና የዲጂታል ቦርሳ እንቅስቃሴዎችን በቅርብ እንዲከታተል ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን፣ መንግሥት ከቁጥጥር ውጭ የቆየውንና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የዲጂታል ንብረት ገበያ ወደ ታክስ ሥርዓቱ ለማስገባት አልሟል።
በዚህም ግብይቶች ያለ ስም መከናወናቸውን በማስቀረት፣ እንደ ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ሁሉ የክሪፕቶ ተቋማትም የሪፖርት ግዴታ እንዲኖርባቸው በማድረግ ግልጽነትን ለመፍጠር ታስቧል።
የኬንያ ባለሥልጣናት ግምት መሠረት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የክሪፕቶ እንቅስቃሴ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2021 እና 2022 መካከል ብቻ 2.4 ትሪሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 18.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ግብይት ተካሂዷል።
ይህ የግብይት መጠን የአገሪቱን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ወደ አንድ አምስተኛ የሚጠጋውን ድርሻ ይይዛል። አዲሱ የኬንያ እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም ሳይጠቅሱ የሚደረጉ የክሪፕቶ ግብይቶችን ለመቆጣጠርና የንግድ ትርፍን ከታክስ ለመደበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ለመግታት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተጠቁሟል።@seco


