የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚከናወኑ የምክክር ሥራዎችን በያዝነው ሳምንት እንደሚጀምር አስታወቀ። የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በመጪው ጥር ወር መጨረሻ 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድም ተገልጿል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ተግባራት በዚሁ ሳምንት ይጀምራሉ።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሥራው የሚሳተፉ ሰዎችን የመመልመልና የማሰልጠን ሥራዎች ቀድመው እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልል የሚከናወነው የምክክር ሂደት እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ይህም መላ ሀገሪቱን ያካተተ የምክክር መድረክ ለመፍጠር ለተያዘው ግብ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ እስከ የካቲት አጋማሽ 2018 ዓ.ም ድረስ መሆኑን ያስታወቁት ፕ/ር መስፍን፤ ታሪካዊው ዋና ጉባዔ የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት በጥር ወር መጨረሻ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
በዚሁ ጉባዔ ላይ ከመላ ሀገሪቱ የተወከሉ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉም ተጠቁሟል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አጀንዳዎችን የማሰባሰብና ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራዎችን ማጠናቀቁ ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነዉ።@seco


