የዓለም ሁለተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና፣ የቀነሰውን የወሊድ መጠን ለማነቃቃት በሚል ካለፈው ጥር 1 ጀምሮ በእርግዝና መከላከያ መሣሪያዎች እና መድኃኒቶች ላይ የ13 በመቶ የሽያጭ ታክስ መጣሏን አስታወቀች። በአንጻሩ የሕፃናት ክብካቤ አገልግሎቶች ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ መወሰኑ ተገልጿል።
ይህ አዲስ የግብር ማሻሻያ እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ ቻይና “የአንድ ልጅ ፖሊሲን” በምታስገድድበት ወቅት የነበሩ የነፃ መብቶችን የሚያነሳ ነው። አዲሱ ሕግ ከሕፃናት ክብካቤ በተጨማሪ፣ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች እና የአረጋውያን ክብካቤ ተቋማት ከተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ነፃ እንዲሆኑ ይደነግጋል።
ይህም ቤጂንግ ወጣቶች እንዲጋቡ እና ልጅ እንዲወልዱ ለማበረታታት ከምታደርገው ጥረት አካል መሆኑ ተጠቁሟል።
የቻይና መንግሥት ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ቀንሷል። እ.ኤ.አ. በ2024 የተመዘገበው የ9.54 ሚሊዮን ሕፃናት ልደት፣ ከዐሥር ዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በግማሽ የቀነሰ ነው።
ይሁን እንጂ እንደ ኮንዶም እና የእርግዝና መከላከያ ክኒኖች ባሉ ምርቶች ላይ የተጣለው ታክስ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን እና ትችትን አስከትሏል።
በርካታ ዜጎች በማህበራዊ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት፣ ልጅ የመውለድ ውሳኔ ከእርግዝና መከላከያ ዋጋ በላይ በኢኮኖሚ አቅም እና በወደፊት ተስፋ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል። “የአንድ ኮንዶም ዋጋ መጨመር እና ልጅን የማሳደግ ወጪ ሰማይና ምድር ናቸው” ሲሉ ተችተዋል።
በቤጂንግ የሚገኘው የዩዋ (YuWa) የሕዝብ ጥናት ተቋም እ.ኤ.አ. በ2024 ባወጣው ሪፖርት፣ ቻይና ልጅ ለማሳደግ በዓለም ውድ ከሆኑ ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሷል።
ከፍተኛ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የቤት ኪራይ ቀውስ እና ሴቶች በሥራ እና በልጅ አስተዳደግ መካከል የሚገጥሟቸው ጫናዎች ለወሊድ መጠን መቀነስ ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል።@SECO


