በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ጀሎ እና ዶርባዴ ከተባሉ ቀበሌያት ተፈናቅለው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ወደ ቀደመ ቦታቸው ባለመመለሳቸው ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ገለጹ።
ቁጥራቸው 12 ሺህ 182 የሆኑት እነዚህ ነዋሪዎች በ2009 ዓ.ም በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት መፈናቀላቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ እየኖሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ወደ ቦታቸው ለመመለስ ላቀረቡት ጥያቄ መንግሥት እስካሁን ተግባራዊ ምላሽ አልሰጠንም ብለዋል።
ለችግሩ መፍትሔ ያጣነው ሁለቱ አዋሳኝ ክልሎች (ደቡብ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ) ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ በበኩላቸው፣ ክልሎቹ ትኩረት አልሰጡም የሚለውን ወቀሳ አይቀበሉትም። ይልቁንም ተፈናቃዮቹን በተያዘው ዓመት ወደ ቀደመ ቦታቸው ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም የፀጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ ለማድረግ በኮሬ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች መስተዳድሮች መካከል መግባባት ላይ መደረሱንና ጥምር የሰላም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመተካት የግንባታ ቁሳቁሶች እየተሰበሰቡ መሆኑንና ከክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መገባቱን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።@SECO


