ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (Artificial Intelligence) ብቻ የሚያስተምር ልዩ ዩኒቨርሲቲ ልትገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የመንግሥት ዕቅድ ይፋ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት ገለጻ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በዋናነት በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በማሽን ለርኒንግ (Machine Learning)፣ በሮቦቲክስ፣ በዳታ ማይኒንግ እና በኮምፒዩቲንግ የትምህርት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ተቋሙ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት እንዲችልም በየዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው የሚያልፉ 200 ያህል ተማሪዎችን ብቻ እንደሚቀበል ተጠቁሟል።
ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አህጉራዊ ፋይዳ እንዲኖረው ታስቦ የተመሠረተ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ዩኒቨርሲቲው ለእያንዳንዱ አፍሪካዊ አገር ሁለት የነፃ ትምህርት ዕድል እንደሚሰጥም አስታውቀዋል። ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቴክኖሎጂ መሪ ለመሆን ለያዘችው ግብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተነግሯል።@SECO


