የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ለንግድ የዲጂታል ስርጭት ስርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን ከኑኮር ቴክኖሎጂስ ጋር ስልታዊ ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ።
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የተፈረመው ይህ ስምምነት፣ የጉዞ ወኪሎች እና የድርጅት ደንበኞች የአየር መንገዱን የሽያጭ መረጃዎች በቀጥታና በዘመናዊ መንገድ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
በዚህ አዲስ አጋርነት አማካኝነት የአየር መንገዱ የጉዞ ወኪል ፖርታል (Agency Portal) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ2,000 በላይ ንቁ ደንበኞቹን ይበልጥ ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለማገልገል ያስችለዋል።
ስርዓቱ የላቀ የሪፖርት እና የትንታኔ መረጃዎችን የሚያቀርብ ከመሆኑም በላይ፣ የተለያዩ የክፍያ አማራጮችን፣ የሆቴል ፓኬጆችን እና ተጨማሪ አገልግሎቶችን በዲጂታል አማራጭ ለማቅረብ ያግዛል።
በሌላ በኩል በሞዛምቢክ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ “ፋስትጄት ሞዛምቢክ” የአገር ውስጥ በረራዎችን ለመጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከሀገሪቱ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ማግኘቱ ተሰምቷል። በሞሮኮ በኩል ደግሞ ሮያል ኤር ማሮክ በ2026 ቢያንስ 10 አዳዲስ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች በረራዎችን ወደ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ለመጀመር ማቀዱን ይፋ አድርጓል።@SECO


