የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጡ የሳይበር ጥቃቶችንና የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመከላከል ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሚጠቀም አዲስ የደኅንነት ስትራቴጂ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
ባንኩ ይህንን የገለጸው “የእርስዎ እርካታ፣ የባንካችን ስኬት!” በሚል መሪ ቃል ዓመታዊ የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ባካሄደበት ወቅት ሲሆን፣ የባንኩ ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ባስተላለፉት መልእክት ባንኩ ለዲጂታል ደኅንነት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳዩ ቁልፍ ነጥቦችን ዘርዝረዋል።
ለዚሁ ተግባር ስኬታማነት ባንኩ የሳይበር ደኅንነት አስተዳደር መዋቅሩን በምክትል ፕሬዝዳንት ደረጃ ወደሚመራ ክፍል ከፍ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል።

የሳይበር ደኅንነት ክፍሉ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠራበት የ”ዜሮ ትረስት” (Zero Trust) ደኅንነት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ይህ ስትራቴጂ አዳዲስ የሳይበር ሥጋቶችን አስቀድሞ ለመለየት፣ ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በዋናነት ይጠቀማል።
በአሁኑ ወቅት ከ90% በላይ የሚሆነው የባንኩ ጠቅላላ ግብይት የሚከናወነው በዲጂታል አማራጮች በመሆኑ፣ ይህ የደኅንነት ጥበቃ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ባንኩ ከ400 በላይ የሦስተኛ ወገን አገልግሎቶችን በክፍያ አማራጮቹ ውስጥ ማካተቱ የደኅንነት ሥጋቱን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል።
የደኅንነት መሠረተ ልማቱን ማጠናከር በደንበኞች ዘንድ ያለውን ከፍተኛ እምነት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚረዳ የተገለጸ ሲሆን፣ ባንኩ ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርገው የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥና በዲጂታል ግብይት ወቅት የሚታዩ የማጭበርበር ድርጊቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መሆኑን አቶ ኤፍሬም መኩሪያ አረጋግጠዋል።@SECO


