የኢትዮጵያ መንግስት በገጠር አካባቢዎች የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን እና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል የ110 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ድጋፍ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ማግኘቱን አስታወቀ።
ይህ ግዙፍ የፋይናንስ ድጋፍ በዋናነት ለገጠር ፋይናንስ እና ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን፣ በገጠር የሚገኙ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ የተዘጋጀ ነው።
በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይህንን የገንዘብ ድጋፍ ለገጠር የፋይናንስ ተቋማት፣ ለጥቃቅን ፋይናንስ ተቋማት እና ለገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራት በማሰራጨት ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ያደርጋል ተብሏል።
ይህም አርሶ አደሮች እና በገጠር የሚገኙ ነጋዴዎች ስራቸውን ለማስፋፋት የሚያስፈልጋቸውን የካፒታል እጥረት እንደሚቀርፍላቸው ተስፋ ተጥሎበታል።
ይህ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ድጋፍ በተጨማሪ አጋሮች ከሚሰጡት እርዳታ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) እና የአውሮፓ ህብረት (EU) ለዚሁ ፕሮጀክት ስኬት ተጨማሪ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል።@SECO


