የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ፣ ወደ ውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን መብትና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የፕሮጀክቱ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ)፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌደሬሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ይህ በቅድመ-ጉዞ እና በድኅረ-ጉዞ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ፕሮጀክት፣ የምልመላና የቅጥር ሒደት ግልጽነት ባለውና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን በማድረግ የምልመላ ሥርዓቱን የማዘመን ዓላማ ሰንቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የስምሪት መረጃዎችን በአግባቡ በመያዝ ክትትልና ቁጥጥርን ለማጠናከር እንዲሁም ዜጎች በውጭ አገር ቆይታቸው መብቶቻቸው ተከብሮ ከማንኛውም ብዝበዛ እንዲጠበቁ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፉን ያቀረበ ሲሆን፣ የዓለም ሥራ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱን የሚመራው ይሆናል።@SECO


