ቻይና አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ለመውጣት የወሰደችውን እርምጃ በፅኑ በመተቸት፣ አገራት የውስጥ ፖለቲካቸውን ከአለም አቀፍ ህግጋት ማስቀደም የለባቸውም ስትል አስጠነቀቀች።
በጄኔቫ በተካሄደ የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብሰባ ላይ የቻይና ተወካይ እንደገለጹት፣ አገራት ድርጅቱን ሲመቻቸው የሚጠቀሙበት፣ ሳይመቻቸው ደግሞ ጥለውት የሚወጡት ተቋም ሊሆን አይገባም።
በተለይም በትራምፕ አስተዳደር እየተመራች ያለችው አሜሪካ ፣ ከድርጅቱ የመውጣት ሂደቷን ያጠናቀቀች ብትሆንም፣ ድርጅቱ ግን አባል አገራት በምን መልኩ መውጣት እንደሚችሉ ግልጽ የሆነ ደንብ ስለሌለው ጉዳዩን ለዓለም ጤና ጉባኤ መርቶታል። አሜሪካ የቆየባትን የ278 ሚሊዮን ዶላር መደበኛ ክፍያና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የተስፋ ቃል እርዳታ ሳትከፍል መውጣቷም በስብሰባው ላይ በሰሜን ኮሪያ በኩል ተቃውሞ አስነስቷል።
በሌላ በኩል እንደ አርጀንቲና ያሉ የአሜሪካ የቅርብ አጋር አገራትም ተመሳሳይ ውሳኔ እያሳለፉ ሲሆን፣ የእስራኤል ተወካይ ግን አገራት የመውጣት ሉዓላዊ መብት አላቸው በሚል የአሜሪካን ውሳኔ ደግፈዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አያያዝ ዙሪያ ድርጅቱን የከሰሰችው አሜሪካ፣ ከድርጅቱ ብትወጣም ከሌሎች አገራት ጋር በሁለትዮሽ ስምምነት የጤና ደህንነትን እንደምትጠብቅ ገልጻለች።
ሆኖም ቻይና ይህን እርምጃ የዓለም አቀፍ ጤና አስተዳደርን የሚንድ ነው ስትል የከሰሰች ሲሆን፣ በድርጅቱ ውስጥ ያላትን የፋይናንስ ድጋፍ እንደምትጨምርም አስታውቃለች።
አሜሪካ በ1948 ባወጣችው የጋራ የኮንግረስ ውሳኔ መሠረት ከአንድ ዓመት ቅድመ ማስጠንቀቂያ በኋላ መውጣት የምትችልበት ልዩ ፈቃድ ቢኖራትም፣ ለሌሎች አገራት ግን እንዲህ ዓይነት መብት በድርጅቱ መመሥረቻ ሰነድ ላይ አለመካተቱ የሕግ ውዝግብ አስነስቷል።@SECO


