ኢትዮጵያውያን በውጭ አገር ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተፈቀደ

በኢቢቪ ዘጋቢ

በሰፊ የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ጋር ተያይዞ በርካታ ማሻሻያዎችን ማድረጓን ቀጥላለች፡፡ ከነዚህም መካከል ከዚህ በፊት ይተገበሩ የነበሩ ክልከላዎች ማላላት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

መንግስት በቅርቡ ለአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደገለጸው በዛሬ እለት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አማካኝነት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ በርካታ ህጎችን አላልቷል፡፡

ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን ይዘው በመውጣት በውጭ ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ የሚያደርገው ታሪካዊ ውሳኔ ይገኝበታል፡፡

በቀደመው ዘመን ከሃገር ሃብት ማውጣት የማይፈቀድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በህገወጥ መንገድ ከፍተኛ የአገር ሃብት ወደ ውጭ መውጣቱ አልቀረም፡፡

አዲስ የወጣው ህግ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ገንዘባቸውን ይዘው በመውጣት በሌሎች አገራት አትራፊ በሆኑ ቢዚነሶች ተሳትፈው ሃብት ወደ ሃገር መመለስ የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር ነው፡፡

ኢትዮጵያን ቢዝነስ ቪው የተመለከተው የብሄራዊ ባንክ የመመሪያ ማሻሻያ አንቀጽ 4 እንደሚገልጸው ወደ ውጭ ገንዘብ ይዘው ወጥተው ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ በብሄራዊ ባንክ ፍቃድ ሊያገኙ ይገባል፡፡

በዛሬው እለት ብሄራዊ ባንክ ያነሳቸው ክልከላዎች ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር የተደረሰውን ስምምነትና የድርጅቱን የአሰራር ደንብ አንቀጽ 8 ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ፣ በውጭ ምንዛሪ አሰራር ላይ  የነበሩ የቁጥጥር ቅድመ-ሁኔታዎችንና ክልከላዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያላላ ነው፡፡

ማእከላዊ ባንኩ ዛሬ የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደገለፀው ፣ ማሻሻያው ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የተሟላ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም ይበልጥ ለማጎልበትና የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ነፃ፣ ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ ነው።

በአዲሱ መመሪያ መሠረት ግለሰቦችና ቤተሰቦች በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ ሰፊ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል። ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ ሂሳብ ያለው ግለሰብ አስፈላጊውን ሕጋዊ ሰነድ በማቅረብ፤ ለትዳር አጋሩና ለልጆቹ የትምህርት፣ የሕክምና እና የጉዞ ወጪዎችን ካለው የውጭ ምንዛሪ ሂሳብ መክፈል ይችላል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው እስከ 3,000 የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ እንዲልኩ የተፈቀደ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የውጭ ምንዛሪ ቁጠባ ሂሳብ ለመክፈት እንደ ቅድመ-ሁኔታ ይቀመጥ የነበረው የ100 ዶላር አነስተኛ ተቀማጭ ሙሉ በሙሉ ቀርቷል።

የአገልግሎት ዘርፍ ላኪዎችን ለማበረታታት ይረዳ ዘንድ፣ ከሥራቸው የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ መቶ በመቶ በራሳቸው ሂሳብ ውስጥ ያለምንም የጊዜ ገደብ እንዲይዙ ተፈቅዶላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የንግድ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የውጭ ሀገር ክፍያና የኤሌክትሮኒክ ግብይትን የሚያቀላጥፍ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ እንዲያዘጋጁ ፈቃድ ተሰጥቷል።

ይህ ሰፊ የማሻሻያ እርምጃ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ፣ ሕጋዊ የገንዘብ ዝውውርን በማበረታታት ጥቁር ገበያን ለመዋጋትና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር ለማስማማት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የብሔራዊ ባንክ መግለጫ ያመለክታል።©SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 220 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ አወጣ

​የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘጠኝ ክፍለ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

Popular Categories