የኢትዮጵያ መንግሥት እና የልማት አጋሮች ቡድን በአዲስ አበባ ባካሄዱት ከፍተኛ የልማት ፎረም፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ ለአካታች ዕድገትና ለዘላቂ ሰላም በጋራ ለመሥራት የነበራቸውን ስትራቴጂካዊ ጥምረት ማደሳቸውን አስታወቁ።
ውይይቱም በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም “አካታችና ዘላቂ ልማት” እንዲሁም “ብሔራዊ ምክክርና የሰላም ግንባታ ሂደት” ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአማካይ የሰባት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም መንግሥት በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በሰው ሀብት ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ መዋቅራዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በ2024/25 የ9.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧንና በ2025/26 ደግሞ ይህ ዕድገት ወደ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የCOP32 ዝግጅትና የአየር ንብረት አጀንዳ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ፣ ኢትዮጵያ በ2027 ለምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) እያደረገች ያለውን ዝግጅት አስረድተዋል። ጉባኤው የአፍሪካን የአየር ንብረት አጀንዳ ለማስፈጸም እና በአረንጓዴ ልማት ላይ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።@SECO


